ቶሬስ፡ ግሪዝማን እንደመሲና ሮናልዶ ለመቆጠር ዋንጫ ብቻ ያስፈልገዋል

እንደፈርናንዶ ቶሬስ ሃሳብ መሰረት ከሆነ የአትሌቲኮ ማድሪዱ ኮከብ አንቱዋን ግሪዝማን እንደሊዮኔል መሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለመቆጠር ዋንጫ ብቻ ያስፈልገዋል።

ግሪዝማን ባለፈው የውድድር ዘመን ላይ ያስቆጠረውን ያህል በሁሉም ውድድሮች ላይ 26 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ በዚህ የውድድር ዘመንም በአትሌቲኮ ማድሪድ ድንቅ ጊዜ ማሳለፍ ችሏል።

አትሌቲኮ ማድሪድ የላ ሊጋ ዋንጫውን ማንሳት በቻለበት የውድድር ዘመን ክለቡን መቀላቀል የቻለው ፈረንሳያዊው ተጫዋች ስሙ ከባርሴሎና ጋር ተያይዞ ይገኛል።

እንደክለብ አጋሩ ቶሬስ እምነት ከሆነም የ27 ዓመቱ ግሪዝማን ተጨማሪ ዋንጫዎችን ማንሳት ከቻለ እንደሮናልዶ እና መሲ ሁሉ በብዙዎች ዘንድ የሚነገርለት ተጫዋች ይሆናል።

“በመሲ እና ሮናልዶ ደረጃ ለመቆጠር የዋንጫ ድል ብቻ ይቀረዋል።” ሲል ቶሬዝ ለስፔኑ ካዴና ሰር ገልፅዋል።

ቶሬስ አክሎም “እነዚያንም [ዋንጫዎች] በአትሌቲኮ እንደሚያገኛቸው ተስፋ አለኝ።” ሲል ገልፅዋል።

የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ አትሌቲኮ ማድሪድን እንደሚለቅ በይፋ ያሳወቀው ፈርናንዶ ቶሬስ ግሪዝማን፣ ግብ ጠባቂው ያን ኦብላክ እና አሰልጣኙ ዲያጎ ሲሞኒ በክለቡ እንዲቆዩ ፍላጎቱ መሆኑንም ገልፅዋል።

“እኔ ፈፅሞ ከኦብላክ የተሻለ ግብ ጠባቂ አይቼ አላውቅም።” በማለት “እንዲቆይ ለማድረግም ማንኛውንም ክፍያ እከፍላለሁ።” ሲል ገልፅዋል።