የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር በአሎንሶ ላይ ክስ መሰረተ

የቼልሲው ማርኮስ አሎንሶ ፈፅሟል በተባለው ከባድ የጨዋታ ላይ ጥፋት በእንግሊዝ የእግርኳስ ማህበር ክስ ተመስርቶበታል።

የግራ መስመር ተከላካዩ በእሁዱ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በሳውዛምፕተኑ አጥቂ ሼን ሎንግ ጀርባ በኩል ኃይለኛ አጨዋወት ሲፈፅም የታየ ቢሆንም፣ በወቅቱ የጨዋታው ዳኛ በነበሩት ማይክ ዲን ምንም አይነት ቅጣት አልተወሰነበትም።

ይሁን እንጂ የእግርኳስ ማህበሩ የስፔናዊውን ተጫዋች ድርጊት የሚያሳየውን ቪዲዮ ዳግመኛ ተመልክቶ ክስ በመመስረት ተጫዋቹ በጉዳዩ ላይ እስከረቡዕ ምሽት 3 ሰዓት ድረስ ምላሽ እንዲሰጥ ቀነ ገደብ አስቀምጧል።

አሎንሶ ክሱን የሚቀበል ከሆነ ከሳውዛምፕተን ጋር የሚደረገውን የእሁዱ የኤፍኤ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜን ጨምሮ በፕሪሚየር ሊጉ ሃሙስ ከበርንሌይ እንዲሁም ቅዳሜ ከስዋንሲ ጋር የሚደረጉት ጨዋታዎች የሚያመልጡት ይሆናል።

Advertisements