ማርሺያል በዩናይትድ መንታ መንገድ ላይ ይገኛል

የአሌክሲስ ሳንቼዝ ኦልትራፎርድ መድረስ ለአንቶኒ ማርሺያል ከመጀመሪያ ተመራጭ ተጫዋችነት ውጪ እንዲሆን ገፊ ምክኒያት ነበር። ይህ ደግሞ የተጫዋቹን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ ያደርግው ይመስላል። ታዲያ ተጫዋቹ ክለቡን የሚለቅበት ጊዜ አሁን ይሆን? ተከታዩ ፅሁፍ ተጫዋቹን የተመለከት ዝርዝር ትንታኔ ይዟል።

ማንችስተር ዩናይትድ በጥር ወር አሌክሲ ሳንቼዝን ከአርሰናል ማስፈረሙን በይፋ ሲገልፅ የአንቶኒ ማርሺያል ብቃት በአስደናቂ ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር። ፈረንሳያዊው ተጫዋች ከዚያ ቀደም ባሉት ጊዜያት በኤቨርተን፣ በስቶክ እና በርንሌይ ክለቦች ላይ ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ግቦችን በማስቆጠር ችሎ ለዩናይትድ የግራ ክንፍ ስፍራ ብቁ መሆኑን ደጋፊውን ማስደሰት ከመቻሉም በላይ የጆዜ ሞሪንሆን ቀልብ መሳብም ችሎ ነበር።

የተጫዋቹ አጨዋወት ለሞሪንሆ እንቅቆቅልሽ እንደሆነ ቢገኝም፣ ነገር ግን ሳንቼዝ በተቀያሪ ወንበር ላይ ሳይቀመጥ ጎላ ያለ የመጫወት ዕድል ተሰጥቶታል። ቺሊያዊው ተጫዋች ማርሺያል ወደቀኝ ክንፍ እንዲዞር ተደርጎ የግራ ክንፍ የማጥቃቱ ሚና የተሰጠውም ወዲያውኑ ክለቡን ከረገጠበት ጊዜ አንስቶ ነበር። መልዕክቱ ደግሞ ግልፅ ነበር። ይኸውም ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ማርሺያል ከሳንቼዝ ቀጥሎ ተመራጭ የሚሆን ተጫዋች መሆኑ ነው።

ይህ አዲሱ ቦታው ደግሞ ማርሺያል ጠንካራ በሆነበት ተፈጥሯዊ እግሩ ሰብሮ መግባት እንዲችል ሊያደረገው ባለመቻሉም የቀደመ ሚናው እንዲገታና አቋሙ እንዲወርድ ምክኒያት ሆኗል። እንዲሁም ክለቡ በቶተንሃም እና ኒውካሰል በተከታታይ ሽንፈት የደረሰበት መሆኑን ተከትሎ በቡድኑ ውስጥ የነበርውን የመጫወት ዕድል ለማጠት ተገዷል። ዩናይትድ ቼልሲን 2ለ1 መርታት በቻለበት ጨዋታ ላይ ተመልሶ በመጫወት የዩናይትድን የመጀመሪያዋን ግብ ሉካኩ እንዲያስቆጥር ማድረግ ቢችልም፣ ከሰባት ጨዋታ ግን የመጀመሪያ ተሰላፊ መሆን የቻለው በአንዱ ላይ ብቻ ነበር።

ዩናይትድ ረቡዕ (ዛሬ) ምሽት ወደቦርንማውዝ አቅንቶ በሚያደረገው ጨዋታ ሌላ የመሰለፍ ዕድል ያገኝ ይሆን? ዩናይትድ በዌስት ብሮም በደረሰበት አስደንጋጭ ሽንፈት ምክኒያት የተጫዋች ለውጥ እንደሚያደርጉ ቃል የገቡት ሞሪንሆ ሳንቼዝን እና ፓል ፖግባን ከቡድኑ እንደሚቀንሱም ገልፀዋል። ነገር ግን በእሁድ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ማርሺያል ወደመጀመሪያ ተሰላፊነት ስለመመለሱ ጉዳይ እርግጥ የሆነ ሃሳብ መስጠት ይቸግራል።

ጋዜጦች በዩናይትድ የሚኖረው ቆይታ ብዙም እንዳልሆነ መዘገባቸውን ተከትሎም ማርሻል በኦልትራፎርድ የነበረው አቋም እና ፍጥነት እክል የገጠመው ይመስላል። ለ31 ደቂቃዎች ያህል ተሰልፎ በተጫወተበት የእሁድ ዕለቱ ጨዋታ አንድ እንኳ የግብ ሙከራ ማድረግ፣ የግብ ዕድል መፍጠርና የተሳካ ኳስ ማሻማት አልቻለም። ኳስን መልሶ መንጠቅ ሳይችል ለ13 ጊዜ ያህል የኳስ ቁጥጥሩን አበላሽቷል። ሞሪንሆም ቢሆኑ ከጨዋታው በኋላ “ኳስን በቀላሉ ይነጠቃል።” ሲሉም ቡድናቸውን ተችተዋል።

ምንም እንኳ ማርሻል በቦርንማውዙ ጨዋታ ላይ ሌላ ዕድል ቢያገኝም፣ ማንችስተር ዩናይትድ ለእሱ ትክክለኛው ክለብ መሆኑ ላይ ጥያቄ ማንሳቱ የማይቀር ነው። የ22 ዓመቱ ተጫዋች በ57.6 ሚ.ፓውንድ በድንገቴ ግዚ የተገኘ ትጫዋች እንደሆነ የሚተቹትን አፍ በማዘጋት በልዊ ቫን ኻል የአሰልጣኝነት ዘመን በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ አንፀባራቂ ብቃቱን በማሳየት በውድድር ዘመኑ የዩናይትድ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ መጨረስ ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ ያለፈው የውድድር ዘመን ቆይታው ግን በእጅጉ የተለየ ነበር።

በዚያ የውድድር ዘመን ዝላታን ኢብራሂሞቪች የአንቶኒዮ ማርሺያል የመለያ ቁጥር ከመንጠቅ አንስቶ የክለቡ አብይ ተጫዋች ነበር። የሞሪንሆን ፍላጎት ለማሳካት ሲልም ከመጫወቻ ቦታው ተገፎቶ ከቡድኑ ውጪ እንዲሆንም ተደርጓል። ሞሪንሆም እስከዚህኛው የውድድር ዘመን ድረስ “በልጁ ላይ ትልቅ መሻሻል ተመልክቻለሁ። በፊቱ ላይ የሚታየው ስሜት እና አካላዊ ንግግሩም ተሻሽሏል።” የሚል ምለሽ ሲሰጡ ቆይተዋል።

ይህ ሞሪንሆ የሚሉት መሻሻል ግን በሜዳ ላይ አልታየም። ይልቁኑ ማርሻል በሜዳ ላይ የሚጫወትበት ጊዜም ሆነ ብቃቱ በይጊዜው እያሽቆለቆለ መጥቷል። ይሁን እንጂ ተጫዋቹ በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ተሰላፊ መሆን በቻለባቸው 16 ጨዋታዎችና ተቀይሮ በገባባቸው 11 አጠቃላይ ጨዋታዎች ላይ ያስቆጠራቸው ዘጠኝ ግቦች እና ያመቻቻቸው አምስት የግብ ዕድሎች አማካኝ ግብ በሜዳ ላይ በቆየባቸው በ98.2 ደቂቃዎቹ የግብ ተሳትፎ ማድረጉን የሚያመለክቱ ናቸው።

የዓመቱ ምርጥ ተጫዋችነትን እንደሚያነሳ የተሻለ ግምት የተሰጠው መሐመድ ሳለህ፣ የማንችስተር ሲቲ ሁለት ተጫዋቾች ሰርጂዮ አጉዌሮ እና ራሂም ስተርሊንግ እንዲሁም የቶተንሃሙ አጥቂ ሃሪ ኬን ብቻ በዚህ የውድድር ዘመን በግቡ አፋፍ ላይ ስኬታማ የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው። በዚህ ላይ ከማርሺያል የማንችስተር ዩናይትድ የቡድን አጋሮች አንፃር ግን የእሱን ያህል የግብ ማስቆጠርና የማመቻቸት ስኬት መጠጋት እንኳ የቻለ ተጫዋች የለም።

ፍጥነት፣ ክህሎትና አስደናቂ አጨራርስ የማርሺያል ልዩ ችሎታዎች መሆናቸው ግልፅ ነው። በግልፅ የተቀመጡት አሃዘዊ መረጃዎቹም ለምን እንደጁቬንቱስ፣ ፒኤስጂ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ያሉ የአውሮፓ ኃያላን ክለቦች ፈላጊዎቹ እንደሆኑ በሚገባ የሚያሳዩ ናቸው። ነገር ግን ቁጥሮቹ ለምን ተጨማሪ ዕድሎች እንዳለገኘም ጥያቄ ሊያስነሱ ይችላሉ። ማርሺያል ይህን ያህል ግብ ለማስቆጠርና የግብ ዕድሎችን ለማመቻቸት በአንድ የውድድር ዘመን በአንድ ውድድር ላይ በተከታታይ ከሁለት ጨዋታዎች በላይ የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድል ማግኘት ይኖርበታል።

በእርግጥ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድልን ቢያገኝም፣ ነገር ግን ከፊት ለፊቱ ከተደቀነው መሰናክል ባሻገር መመልከት ይቸግራል። ሳንቼዝ በኦልድትራፎርድ ካለው አራት ዓመት ከግማሽ ኮንታርት ገና ጥቂቱን ወር ብቻ ነው የተጫወተው፣ እንዲሁም ኢብራሂሞቪች ክለቡን ቢለቅም የመሃል ተከላካይነቱ ሚና ሞሪንሆ “ሃምሳአለቃ” ላሉት ሉካኩ የተተወ ነው። ጄሴ ሊንጋርድ እንኳ ከእሱም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተጫዋች ይመስላል።

ማርከስ ራሽፎርድ እንኳ ቢሆን ከዕድሜው ለጋነት አንፃር በ20 ዓመት ዕድሜው በክለቡ ብዙም ዕድል ያልተሰጠው ተጫዋች መሆኑ ባይገርምም ነገር ግን በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 23 ዓመት የሞላው ማርሺያል ግን የመጀመሪያ ተሰላፊነት ሚናን ማግኘት የግድ ይለዋል። ይህ ደግሞ የመሰለፍ ዕድል ተስፋውን ከጆዜ ሞሪንሆና ማንችስተር ዩናይትድም ባሻገር እንዲማትር ሊያደረገው የማይችልበት ሁኔታ ያለ አይመስልም።