በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወላይታ ድቻ ወደ ምድብ ድልድሉ መቀላቀል ሳይችል ቀረ

በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመግባት የመልስ ጨዋታውን ያደረገው ወላይታ ድቻ በአጠቃላይ ውጤት 2-1 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆነ።

ወላይታ ድቻ ከ10 ቀናት በፊት የመጀመሪያ ጨዋታውን በታንዛኒያ ዳሬሰላም ስታድየም ከያንግ አፍሪካ ጋር ተጫውቶ 2-0 መሸነፉ ይታወሳል። 

በጥንቃቄ ጉድለት የተቆጠሩት ሁለት የጭንቅላት ኳሶች ተሸንፎ የተመለሰው ድቻ ዛሬ በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም ባደረገው የመልሱ ጨዋታ የመጀመሪያውን ዙር ውጤት ለመቀልበስ ቢጫወትም አጠቃላይ ውጤቱ ወደ ቀጣይ ዙር የሚየሻግረው አልሆነም።

በማጥቃት የጀመሩት ባለሜዳዎቹ በ 3ኛ ደቂቃ ላይ ቶጎዋዊው አጥቂ ጃኮ አረፋት የመጀመሪያውን ጎል በማስቆጠር ድቻዎች መልካም አጀማመር እንዲያደርጉ አድርጓል።

ከጎሉም በኋላም ተጭነው የተጫወተቱት የጦና ንቦቹ ተጨማሪ ጎል የሚያስቆጥሩበትን እድል መፍጠር ችለው ነበር።

በተለይ 19ኛው ደቂቃ ላይ የያንጋው ግብ ጠባቂ ሮስታንድ ጄሁ የግብ ክልሉን ለቆ ከወጣ በኋላ የተሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።

29ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁ በዛብህ መለዩ ወደ ጎል የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በእጁ ከጨረፋት በኋላ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ጃኮ አረፋት ወደ ግብ ቀየራት ሲባል በእግሩ መሀል አልፋ የሄደችው እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ ነበረች።

እንግዳዎቹም ቢሆኑ የድቻ ተከላካዮች መዘናጋት በመጠቀም አልፎ አልፎ የፈጠሩት ጫና 27ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋ ኤልያስ እራሱ ጎል ላይ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።

ግብ ጠባቂው ወንደሰን እና ውብሸት ባለመግባባት ያንጋዎች ያገኙት ጥሩ የጎል አጋጣሚው ወደ ውጪ ወጥቶባቸዋል።

በመስመር ላይ ወደ ሳጥን በማሻማት በጭንቅላት የሚገጩ ኳሶችን ሲፈልጉ የነበሩት ያንጋዎች በ 7ቁጥሩ ኦቤሪ ቺርዋ በመስመር ላይ ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይተዋል።

ለእረፍት ወደ መልበሻ ቤት ከማቅናታቸው ከደቂቃ በፊትም ከማእዘን የተሻማውን ኳስ አብደላ ሻኢቡ ግልፅ እድል በጭንቅላቱ የማስቆጠር አጋጣሚ አግኝቶ ወንደሰን መልሶታል።

ከእረፍት መልስ ተሽለው የመጡት ያንጋዎች በተደጋጋሞ ጥሩጥሩ የጎል እድሎችን መሞከር ችለዋል።

በዚህ የጨዋታ ጊዜ ያሬድ ዳዊት በግራ መስመር አታሎ የሞከረው ኳስ ደግሞ ለባለሜዳዎቹ ሊጠቀስ የሚችል አጋጣሚ ነበር።

በዛብህ መለዩ በጭማሪ ሰአት ላይ ያገኘው ድንቅ አጋጣሚ መረጋጋት ሳይችል የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ድቻ ጨዋታውን 1-0 ቢያሸንፍም በአጠቃላይ 2-1 በመሸነፉ ምክንያት ውጤቱ አንግዳዎቹን ተጠቃሚ በማድረጉ ያንግ አፍሪካ ወደ ምድብ ድልድሉ መቀላቀሉን አረጋግጧል።

ወላይታ ድቻ በውድድሩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመሳተፉ ያስመዘገበው ውጤት የሚበረታታ ሲሆን በተለይም የግብፁን ዛማሌክን በማሸነፍ አስደናቂ ታሪክ መፃፍ መቻሉ የሚዘነጋ አይደለም።

Advertisements