“በ2018 የአለም ዋንጫ ላይ አንድም የአፍሪካ ተወካይ ከሩብ ፍፃሜ በላይ መጓዝ አይችልም ” – ላውረን

የቀድሞ የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን እና የአርሰናል ተጫዋች የነበረው ላውረን በ 2018 የአለም ዋንጫ ላይ የአፍሪካ ተወካዬች አንዳቸውም የሩብ ፍፃሜ በላይ ማለፍ እንደማይችሉ አሳውቋል።

ላውረን በካሜሮን ብሔራዊ ቡድን እና አርሰናል በመስመር ተከላካይ ቦታ ላይ በመጫወት ይታወቅ የነበረ ሲሆን በ 1998 እና በ 2002 የአለም ዋንጫ ላይም ሀገሩን ወክሎ ተሳትፏል። 

ተጫዋቹ ከጥቂት ወራት በኋላ በሚጀመረው የራሺያው የአለም ዋንጫ ላይ ከአፍሪካ ተወካዮች ብዙ ነገር እንደማይጠብቅ አሳውቋል።

በአፍሪካ ውስጥ ያለው የአመራር ክፍተት እንዲሁም በተጫዋቾቹ መካከል ያለው የጥራት ልዩነት አፍሪካን በአለም ዋንጫው ላይ ለሚወክሉት ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ቱኒዚያ፣ግብፅ እና ሞሮኮ እንዲቸገሩ ያደርጋቸው ሲል ሀሳቡን ያብራራል።

“አፍሪካ ግማሽ ፍፃሜ ትገባለች፣ዋንጫም እናገኛለን ማለት እችላለው ነገርግን ያ እውነት አይደለም።

“እውነት ለመናገር አንዳቸውም ቡድኖች ከሩብ ፍፃሜው አልፈው መጓዝ አይችሉም።ይህ የኔ እውነተኛው ግምቴ ነው፤ ምክንያቱም እኛ አሁንም ከትላልቅ ቡድኖች አንድ ደረጃ ወደ ኋላ ቀርተናል።

” አንዳቸውም የአፍሪካ ተወካይ ጀርመንን፣ስፔን፣አርጀንቲናን እና ከብራዚልን መቋቋም አይችሉም።ምክንያቱን በነሱ ደረጃ ላይ የሚገኙ አይደሉም።”

ላውረን በአፍሪካ እግርኳስ እየሄደበት ያለበት መንገድም ደስተኛ እንዳልሆነ ጨምሮ አሳውቋል።

“ህዝቡን ልዋሸው አልፈልግም፣የምናገረው እውነተኛውን እና በጭንቅላቴ የማስበውን ነው።ምክንያቱም በአፍሪካ ነገሮች በትክክለኛው መንገድ እየተጓዙ አይደለም።” ሲል ሀሳቡን ገልፇል።

የአፍሪካ ተወካዮች በአለም ዋንጫው ላይ ሩብ ፍፃሜ የገቡት ሶስት ጊዜ ሲሆን ይኸውም 1990 ላይ ካሜሮን፣2002 ላይ ሴኔጋል እንዲሁም በ2010 የደ/አፍሪካ የአለም ዋንጫ ላይ ጋና እንደነበች ይታወሳል።

በራሺያው የአለም ዋንጫ ላይ ከ 1998 በኋላ ወደ አለም ዋንጫው የተመለሰችው ሞሮኮ ስፔን እና ፖርቹጋል ያሉበት ምድብ ውስጥ ተካታለች።በዚህ ምድብ ውስጥ የምትገኘው ኢራንም በቀላሉ የምትታይ አይደለችም።

ከ 28 አመት በኋላ አፍሪካን በአለም ዋንጫ ላይ ለመወከል የታደለችው ግብፅ ከአዘጋጇ ሀገር ራሺያ፣ሳውዲአረቢያ እና ኡራጋይ ጋር ትፋጠጣለች።

ቱኒዚያም እንዲሁ ቤልጄም፣እንግሊዝ እና ፓናማ ባሉበት ምድብ ጠንካራ ፈተና ይጠብቃታል።

ሴኔጋል ደግሞ ኮሎምቢያ፣ጃፓን እና ፖላንድ ባሉበት ምድብ ውስጥ መካተቷ የሚታወስ ሲሆን ናይጄሪያ እንዲሁ ከአርጀንቲና፣ክሮሺያ እና አይስላንድ ጋር ተደልድላለች።