ኹልዮ ሴዛር ጓንቱን ሊሰቅል ነው

ብራዚላዊው የቀድሞው የኢንተር ሚላን ግብ ጠባቂ ኹልዮ ሴዛር ጓንቱን ለመስቀል የተዘጋጀ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ የመጨረሻ የፕሮፌሽናል እግርኳስ ጨዋታውን ለፍላሚንጎ-አሜሪካ ሚኔሮ የሚያደረግም ይሆናል።

የሴሪ አው ኃያል ክለብ ታሪካዊ ተጫዋች ኹልዮ ሴዛር የፕሮፌሽናልነት ዘመን የመጨረሻ ጨዋታውን አስመልክቶ ከጣሊያኑ ላ ጋዜታ ዴሎ ስፖርት ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል።

“እስደናቂ ዘመን አሳልፌያለሁ። ህልም ነበር። እንዲህ ዓይነቱ አስደናቂ [የእግርኳስ ተጫዋችነት] ዘመን ይኖረኛል ብዬ ፈፅሞ አልሜ አላውቅም። የመጨረሻ ጨዋታዬም ለእኔ እና ለፍላሚንጎ ታላቅ ስጦታ እንደሚሆን እጠብቃለሁ። እነዚህ ደጋፊዎች ከልጅነቴ አንስቶ መልካም አቀባበል ሲያደርጉልኝ ቆይተዋል። ዕድሜዬ ከፍ ሲልም ለበርካታ ዓመታት በአውሮፓ ተጫውቻለሁ። በዚህም እነሱን አመሰግናለሁ።

“ያለጥርጥር የማለቅስ ይሆናል። አኔ አይናፋር አለመሆኔን የኢንተር ደጋፊዎች በሚገባ ያውቁታል። ለካሜራም ግድ አይሰጠኝም። አዎ በሚገባ አለቅሳለሁ።” ሲል ተናግሯል።

ኹልዮ ሴዛር የወደፊት ዕጣ ፈንታውን አስመልክቶም “በእግርኳሱ ዓለም ላይ እቆያለሁ። ነገር ግን እንዴት እና በምን አይነት ሚና እንደሚሆን ግን አላውቅም። የምንጊዜው ምርጥ ኳስ ያዳንኩት? በሻምፒዮንስ ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ የመሲን ሙከራ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ምናልባት ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። ከትልቅ ክለብ ጋር የተደረገ ጨዋታ እና ልዩ የሆነ ጥረት ነበር። እንድን ኳስ ማዳን ውብ የሚሆነው በወሳኝ ሰዓት ሲሆን ብቻ ነው።” ሲል ተናግሯል።

Advertisements