የስታድየም ስርአት አልበኝነት በደቡብ አፍሪካ

ትናንት ምሽት በደቡብ አፍሪካ በደርባን ሞሰስ ማቢዳ ስታድየም የታየው የደጋፊዎች ሁከት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ያስከተለ ሆኗል።

በስታድየም ውስጥ የሚታዩ ሁከቶች አሁንም በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

በኬኒያ፣ታንዛኒያ፣ኢትዮጵያ፣ደ/አፍሪካ እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ ሀገራት ባለፉት አመታት በተደጋጋሚ የስታድየም ረብሻዎች ታይተዋል።

አሁን አሁን ሀገራችንም በስታድየም ረብሻዎች ስማቸው ከሚነሱ ሀገራት ውስጥ ተካታለች።

ለዚህ ደግሞ ከባለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በአ/አ እና በክልል ስታድየሞች እየተፈጠሩ የሚገኙ ረብሻዎችን ማስታወስ ይቻላል።

ትናንት ምሽት እንዲሁ በደ/አፍሪካ ደርባን በሚገኘው የሞይስ ማዲባ ስታድየም የካይዘር ቺፍስ ደጋፊዎች የፈፀሙት ረብሻ እጅግ አሳፋሪ ሆኖ አልፏል።

ካይዘርስ ቺፍስ ባለፉት አመታት ውጤት በማጣት ሲቸገር የቆየ ሲሆን ዘንድሮም ብቸኛ ዋንጫ ሊያገኙበት የሚችሉበት እድልን ትናንት አበላሽተዋል።

በኔድ ባንክ የጥሎማለፍ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በአሸናፊነት ይወጡታል የተባለውን ጨዋታ በፍሪስቴት ስታር ሳይታሰብ 2-0 ተሸንፈው ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።

ውጤቱ ደግሞ በሌሎች ውድድሮች ላይ አሸናፊ የመሆን እድሉ ላከተመው ካይዘርስ ቺፍስ ሌላ አመት ያለ ምንም ዋንጫ እንዲያጠናቅቅ የተገደደበት ሆኗል።

ይህ ደግሞ ክለቡ ከተመሰረተበት 1970 በኋላ ምንም አይነት ዋንጫ ሳያገኝ ለረጅም አመታት ያሳለፈበት አመት በመሆኑ ደጋፊዎቹን አበሳጭቷል።

ከጨዋታው የመጨረሻ የመጠናቀቂያ ፊሽካ በኋላ ብሶት ውስጥ የነበሩት ደጋፊዎች ሜዳውን በመውረር የክለባቸውን ተጫዋቾች እና አሰልጣኙን በማባረር የስታድየሙ ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

ተጫዋቾቹም እራሳቸውን ለማዳን ወደ መልበሻ ቤት ቢያመልጡም ደጋፊዎች ግን የስታድየሙን ወንበሮች ሲሰበሩ እና ሲቃጠሉም ታይተዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በፊትም በተጫዋቾች የተጠባባቂዎች መቀመጫ ላይ ቁሳቁስ ሲወረውሩ የታዩት ስርአት አልበኛ የክለቡ ደጋፊዎች ከፀጥታ አካላት ጋርም ተጋጭተዋል።

(ሊንኩን ተጭነው በቪድዮ ይመልከቱ)

በተለይም አንድ ሴት የፀጥታ ፖሊስ ላይ ጉዳት ሲደርስ የሚያሳዩ ቪድዮዎች ታይተዋል።

ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በደጋፊዎቹ ላይ በመልቀቅ ደጋፊዎች እንዲበተኑ ካደረገ ከሁለት ሰአታት በኋላ ተጫዋቾቹ ከስታድየም ለቀው ሄደዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ካይዘርስ ቺፍስ ከቡድኑን አሰልጣኝ ስቲቭ ኮምፌላ ጋር መለያየቱን አሳውቋል።

ኮምፌላ የ 2015/2016 የውድድር አመት ከመጀመሩ በፊት የወቅቱ የደ/አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ስትዋርት ባክስተርን ተክተው ወደ ቺፍስ አቅንተዋል።

አሰልጣኙ በቆይታቸው 112 ጨዋታዎችን ያደረጉ ሲሆን 47 ጊዜ ሲያሸንፉ፣27 ጊዜ ደግሞ ተሸንፈዋል።በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ የቻሉት ደግሞ 38 ጊዜ ነው።

ስቲቭ ኮምፌላ

142 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ፣የተቆጠረባቸው ደግሞ 114 ነው።አሰልጣኙ በቆይታቸው የማሸነፍ ስኬታቸው 42% ሲሆን ላለፉት ሶስት አመታት ያሸነፉት ዋንጫ የለም።

ተጨማሪ ቪድዮዎች ይመልከቱ

Advertisements