የግብፃዊ ልዕለ ኮከብ፣ ሞ ሳላህ የእግርኳስ ስኬት ጉዞ

ግብፃዊው የሊቨርፑል ልዕለ ኮከብ ቀዮቹን በተቀላቀለበት የመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ የሊጉን የግብ ማስቆጠር ክበረወሰን መጨበጥ ከመቻሉም ባሻገር የፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋቾች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን መቀዳጀትም ችሏል። ተከታዩ ፅሁፍም ከአፍሪካዊቷ ሃግር ግብፅ ሊግ ተነስቶ በዓለማችን ቀዳሚው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለኮከብነት ደረጃ መብቃት የቻለውን መሐመድ ሳላህን የእግርኳስ የውጣ ውረድ ጉዞ በሰፊው ይዳስሳል።

መሐመድ ሳላህ በ36.9 ሚ.ፓውንድ ከኤኤስ ሮማ ሊቨርፑልን ከተቀላቀለበት ያለፈው ክረምት አንስቶ ተሰልፎ መጫወት በቻለባቸው 46 ጨዋታዎች 41 ግቦችን ማስቆጠር ችሎ በሊቨርፑል የአጥቂ ክፍል ላይ ድንቅ የሆነ ተጨማሪ ጉልበት ማከልም ችሏል። በዚህ ድንቅ ድርሻውም የውድድር ዘመኑ የፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋችነት ሽልማትን ማሸነፍ ችሏል።

ነገር ግን በመላው መርሲሳይድ “ግብፃዊው ንጉስ” የሚል ስያሜን ማግኘት ለቻለው ተጫዋች እዚህ መድረስ ህይወት ሁልጊዜም ቀላል አልነበረችም።

የሳላህ የስኬት ታሪክ በቁርጠኝትና በእልህ አስጨራሽ ትግል እንደተገኘ እዚህ ደረጃ እንዲበቃ የረዱት ሰዎች ይመሰክራሉ።

“በአረብ ኮንትራክተርስ (ክለብ) ከ16 ዓመት በታች ቡድኑን ሳሰለጥን አምስት የግራ መስመር ተጫዋቾች ነበሩኝ። ከእነሱ መካከልም እንዱ ሳላህ ነበር።” ሲሉ ይናገራሉ ሳዒድ ኤል-ሺሺኒ።

ኤል ሞካውሉን ኤፍሲ በሚል ስምም ጭምር የሚታወቀው አረብ ኮንትራክተርስ ክለብ ሳላህ በኤል-ሺሺኒ ኣና አሰልጠኝነት በሁለት ዓመት ጊዜ የመጀመሪያውን ፕሮፌሽናል የተጫዋችነት ስልጠና ያገኘበት ክለብ ነው።

“ከ16 ዓመት በታች በአንድ የካይሮ ሊግ በጣም ጠንካራ የወጣቶች ስልጠና ካለው ከኢኤንፒፒአይ ጋር እየተጫውትን ነበር። ሳልህ በግራ ክንፍ የመስመር ተከላካይነት ሚና በተሰለፈበት እና ከአምስት ያላነሱ ጊዜያት ከበረኛ ጋር ብቻ ለብቻ የመገናኘት ዕድል ማግኘት ችሎ በነበረበት ጨዋታ 4ለ0 በሆነ ውጤት አሸነፍን።

“እኔ ግቦችን ያማከነበትን ዕድል ብቻም አልነበረም የተመለከትኩት። ነገር ግን ከግብ ጠባቂው ጋር ብቻ ለብቻ ለመገናኘት ኳስን እየገፋ የሄደበትንም ክህሎትም ጭምር ነበር። ያደረጋቸው ሩጫዎች በሙሉ ጉልበቱን ይጨርሱ ስለነበር የግሽ ዕድሎችን አምክኗል።

“ነገር ግን ከዚህ ጨዋታ በኋላ ሳላህ ባመከናቸው የግብ ዕሎች ምክኒያት ሲያለቅስ ተመለከትኩት። በእምባ ታጥቦ ነበር! ያን ቀን ሶስት ግቦችን ላስቆጠረው ተጫዋቾች 50 የግብፅ ፓውንድ ሰጥቼ ነበር። ለሳላህም 25 ፓውንድ ሰጠሁት።” ሲሉ የቀድሞው የሳላህ የብቃት መስረት የነበሩት ሰው ተናግረዋል።

የሳላህ የእግርኳስ ህይወት ድንገተኛ ለውጥ ማድረግ እንዲችል ምክኒያት የሆነው በሜዳው የኋላ ክፍል በመከላከሉ ሚና ክህሎቱ መባከኑን አሰልጣኙ በመረዳታቸውም ነበር።

“ከዚያን ቀን አንስቶም ሳለህን በቀኝ ክንፍ በኩል ለማጫወት ወሰንኩ።” በማመት ኤል-ሺሺኒ ተናግረው “ከ16 ዓመት በታች የካይሮ ሊግ እና ከ17 ዓመት ብታች ብሄራዊ ሊግ ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እንደሚሆን ነገርኩት። ሁለቱንም ቡድኖች አሰልጥኛለሁ። በሁለቱም ሊጎች ላይ ደግሞ ሳላህ ተጫውቷል።

“በውድድር ዘመኑ መጨረሻ በድምሩ 35 ግቦችን አስቆጠረ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም ፈፅሞ ግብ ሳያስቆጥር ቀርቶ አያውቅም።” ሲሉ ተናግረዋል።

የሳላህ ዕድገት በግብፅዋ ጋርቢያ ግዛት በምትገነው ናግሪግ በተሰኘት ትንሽ መንደር ውስጥ ነበር። ያን ያደርገበትን መንደር መሰረታዊ ማንንነትም እስካሁን እንደያዘ ይገኛል።

“በግብፅ አንድ ተጫዋች በፍጥነት ዝነኛ መሆን ሲጀምር የነበረው ትህትናም አብሮ መለወጥ ይጀምራል። ” ይላሉ ኤልሺሺኒ “ነገር ግን ሳላህ ፈፅሞ የተለወጠ ሰው አልነበረም።

“ሳላህ ሁልጊዜም ወደክለቡ ይመጣ የነበረው ናግሪግ ከተበለቸው መንደሩ ነበር። ጉዞው ደግሞ የሶስት ሰዓት ነበር። ወደእኛ ይመጣ የነበረውም ከአንድ በላይ በሆነ የመጓጓዣ ዘዴ በመጠቀም ነበር። አንዳንድ ጊዜ በክለቡ መመገቢያ ቦታ እንዲቆይ አደረገው ነበር።”

ሳላህ አሁንም ድረስ ወደዚያች መንደር በመሄድ ለነዋሪዎቿ ያለውን ከፍ ያለ አክብሮት ያሳያል።

ግብፅን ወደዓለም ዋንጫ እንድታልፍ ያደረገችውን ግብ ካስቆጠረ በኋላ አንድ ሃብታም የቢዝነሱ ዓለም ሰው አድናቆታቸውን ለመግለፅ ሲሉ ለሳላህ ቅንጡ ቪላ ለመግዛት ጥያቄ አቅርበውለት ነበር።

ሳላህ ግን የቀረበለትን ጥያቄ አልተቀበለም። ይልቁንስ ገንዘቡም ለመንደሪቱ የበጎ ስራ አግልግሎት ላይ እንዲውል በእርዳታ መልክ ሰጥቷል።

ኤል-ሺሺኒ በዚህ አስመልክተው ሲገልፁ “ናግሪግን ፈፅሞ ዘንግቷት አያውቅም ወደግብፅ በመጣ ጊዜ ሁሉ ወደዚያ ይሄዳል። ህዝቡን በሙሉ በአክብሮት ይመለከታል። እሱ ፈፅሞ መሰረቱን አይረሳም። አንዳንድ ተጫዋቾች ይህን የሚዘነጉ መሆናቸው የሚታወቅ ነው።” ብለዋል።

ዲያ ኤል ሳይድ በ2011 የግብፅ ከ20 ዓመት በታች አሰልጠኝ የነበሩ ሲሆን፣ በዘመኑ ልጆችም “የጡት አባት” የሚል ተቀፅላም ወጥቶላቸዋል። መሐመድ ሳላህን ጨምሮ መሐመድ ኤልኒኒ፣ አህመድ ሃጋዚ እና ኦማር ጋቤሬ የተሰኙት ዝነኛ ተጫዋቾች የእኚህ አሰልጣኝ ፍሬ ናቸው።

ይህ የእርሳቸው የቡድን ስብስብም በወጣቶች አፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ኮሎምቢያ ወደተዘጋጀው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ በማለፍ ብቃቱን አሳይቷል።

ኤል ሳይድ ስለቀድሞው ወጣት ተጫዋቻቸው ሲናገሩ “ሳላህ በጣም ከፍ ያለ ተነሳሽነት የነበረው ተጫዋች ነበር። ሁልጊዜም የመማርና የመሻሻል ፍላጎት ነበረው። በዚያ ላይ ትሁት ለቡድን አጋሮቹ እና አሰልጠኞቹ አክብሮት ያለው ከዚህም በላይ በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ ለእግርኳስ እራሱን የሰጠ ተጫዋች ነበር። ” ሲሉ ገልፀዋል።

ተጫዋቹ ከአረብ ኮንትራክተርስ አንስቶ ሊቨርፑል ለመድረስ በባሰል፣ ቼልሲ፣ ፊዮረንቲናና ሮማ ክለቦች ውስጥ ተጫውቶ ማሳለፍ ችሏል።

“ለዚህም ነው የእግርኳስ ህይወቱ ሁልጊዜም ዕድገት የሚያሳየው።” ሲሉ ኤል ሳይድ ይናገራሉ። “አብረሃቸው ከሰራሃቸው አሰልጣኞች በሙሉ ማግኘት የምትችለውን ነገር ሁሉ ለመውሰድ ሞክር ብዬው ነበር። እሱም የርገን ክሎፕን ከመቀላቀሉ በፊት እንደ ሙራት ያኪን፣ ጆሴ ሞሪንሆ፣ ቪንቼንዞ ሞንቴላ እና ሉቺያኖ ስፓሌቲ ካሉ አሰልጠኞች ጋር ሰርቷል። ከእነዚህ አሰልጠኞች ጋር አብሮ በመስራቱ ምክኒያትም መሻሻል አሳይቷል።” በማለት ተናግረዋል።

ሳላህ ለዚህ ደረጃ ከመብቃቱ በፊትም በ2017 የቢቢሲ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች የተሰኘ ሲሆን፣ በክለቡ ያገኘውን እውቅናም በሩሲያው የዓለም ዋንጫ ላይ ወደዓለማቀፋዊ እውቅና የመቀየር ተስፋ አለው።

ከወዲሁም ከፍተኛ ተነሳሽነት የሚፈጥሩለት በግብፅ በርካታ ትውስታዎች አሉት። ከስድስት አመታት በፊት ስለነበረው ቁልፍ ትውስታም ኤል ሳይድ እንዲህ ያስታውሳሉ።

“በ2011 የወጣቶች የአፍሪካ ዋንጫ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስንጫወት ሳላህ ከ10 በላይ ግብ የማስቆጠር ዕድሎችን አምክኗል።” ሲሉ ገልፀው “ምንም እንኳ በጨዋታው ወደግማሽ ፍፃሜ ማለፍ ብንችልም እሱ ግን ከጨዋታው በኋላ ስቅስቅ ብሎ አልቅሷል።

“ጨዋታው ካለፈ በኋላ ወደልምምድ ሜዳ ወስጄው በባዶ የግብ መረብ ላይ ኳሷን እንዲያዘንብ አደረግኩት። የቡድን አጋሮቹም ከውጪ ሆነው እሱን ለማስደሰት አድናቆታቸውን ገለፁለት።

“የሳላህን የእግርኳስ ህይወት በቅርበት የሚከታተሉ ሁሉ የአጨራረስ ብቃቱን በእጅጉ ማሻሻሉን ያውቃሉ። እሱ ተጫዋቾችን አታሎ በማለፍ ግብ የማስቆጠር ዕድል ላይ ይገኝና ትክክል ያለውን ውሳኔ ይወስናል። ነገር ግን ቀላል የሚባሉ ዕድሎችን ያመክን ነበር። ይህን ለመለወጥም ብዙ ጥሯል። ያንም ማድረግ ችሏል።” ሲሉ የተጫዋቹን የአጨራረስ ለውጥ ገልፀዋል።

ሳላህ አቅሙን አውጥቶ ለመጠቀም ቀላል የማይባል የህይወት ዘመን የትግል ጉዞ አድርጓል።

እናም አሁን ህልሙ እውን እየሆነ ይገኛል። የግብፅ ቀጣዩ ትውልድም እሱን አርዓያ የሚያደረጉ ስለመሆናቸው የሚጠራጠር አይኖርም።

Advertisements