ሊቨርፑል ከ ሮማ፡ የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ

ሊቨርፑል በሊሩ የዓመቱ ኮከብ የተሰኘውን ተጫዋቹን የቀድሞ ክለቡን እንዲገጥም በቡድኑ ውስጥ አካቶ በሻምፒዮንስ ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬ (ማክሰኞ) ምሽት በአንፊልድ ሮማን ይገጥማል።

የኢዩሴቢዮ ዲ ፍራንሲስኮው ቡድን በመጀመሪያ ጨዋታው በባርሴሎና የደረሰበትን የ4ለ1 ሽንፈት በስታዲዮ ኦሎምፒኮ ስታዲይም በመልሱ ጨዋታ በአስገራሚ ሁኔታ 3ለ0 በሆነ ውጤት በመቀልበስ የግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል ችሏል።

ሊቨርፑል


ሊቨርፑል የመሐመድ ሳላህ የብቃት ማንሰራራትን ተጠቅሞ በውድድር ዘመኑ ድንቅ ጉዞ በማድረግ ከ2007 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊጉን የግማሽ ፍፃሜ መቀላቀል ችሏል።

የርገን ክሎፕ ማንችስተር ሲቲን በሩብ ፍፃሜ በደርሶ መልስ ውጤት 5ለ1 ማሸነፍ የቻሉበትን ውጤት ጨምሮ በጥሎ ማለፍ ውድድሮች ላይ በእጅጉ አደገኛ ነበሩ።

የክሎፕ የአጥቂ ክፍል ከፍተኛ ትኩረትን ስቦ በሚገኘው እና በ33 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች 31 ግቦችን በማስቆጠር እንደ ክርስቲያኖ ሮናልዶና አለን ሼረር ያሉ ተጫዋቾች የያዙትን ክብረወሰን ለመስበር አንድ ግብ ብቻ በቀረው ግብፃዊው የፊት ተጫዋች ሳላህ ላይ የተመሰረተ ነው። ይኸው ተጫዋች አሁን ደግሞ ባለፈው ክረምት የለቀቀውን ክለብ የሚገጥምም ይሆናል።

ሊቨርፑል ሮማን ዛሬ ከመግጠሙ በፊት ባደረጋቸው የሊግ ጨዋታዎች ቦርንማውዝን 3ለ0 መርታት ቢችልም ባለፈው የሳምንቱ ማጨረሻ ግን ከሊጉ ላለመውረድ ከሚንገታገተው ዌስትብሮም ጋር በአቻ ውጤት አጠቀናቋል።

ሊቨርፑል በአውሮፓውያኑ አበይት የክለቦች ውድድር ላይ ግን በዚህ የውድድር ዘመን በ12 ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት አልደረሰበትም። ለመጨረሻ ጊዜ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ደግሞ በሰባቱ ላይ በትንሹ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ከእንዚህ ጨዋታዎች ደግሞ በአራቱ ላይ መረቡን አላስደፈረም።

ክሎፕ በባርሴሎና ላይ የደረሰውን ከባድ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሮሙን ክለብ በአንፊልድ ሲገጥሙ ቀላል ግምት እንደማይሰጡት ይጠበቃል።

ወቅታዊ ውጤቶች (በሁሉም ውድድሮች)፡ ድል፣ አቻ፣ ድል፣ ድል፣ ድል፣ አቻ

ሮማ


የዲ ፍራንሲስኮው ቡድን በባርሴሎና የደረሰበትን የ4ለ1 ሽንፈት በመልሱ ጨዋታ ወደ3ለ0 ድል በመቀየር የውድድሩን የምንጊዜውም ድንቅ የውጤት የመቀልበስ ድል ፈፅሞ እዚህ ዙር ላይ ደርሷል።

የጣሊያኑ ክለብ በዚህ ውድድር ላይ ከሜዳው ውጪ ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች የተሸነፍ ሲሆን፣ በዚህም መጥፎ የሚባል ክብረወሰን አለው። ይሁን እንጂ ዲ ፍራንሲስኮ በመልሱ ጨዋታ በስታዲዮ ኦሎምፒኮ መልካም ውጤትን በእጃቸው ለማስገባት ሲሉ በአንፊልድ የሚያደረጉትን ይህን ጨዋታ በእጅጉ ጠበቅ አድረገው እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።

በቀደሙት ጊዜያት ጂያሎሮሲዎቹ የእንግሊዝ ክለቦች በእጅጉ ይፈትኗቸዋል። ሮማ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ከማሸነፉ ውጪ በእንግሊዝ ምድር ላይ ያደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። ሮማዎች በ1984 በዚሁ የአውሮፓውያኑ ዋንጫ ፍፃሜ በፍፁም ቅጣት ምት በሊቨርፑል 4ለ2 የተሸነፉበትን ጨዋታም አይዘነጉትም።

ኤዲን ጄኮ በዚህ የውድድር ዘመን ላይ ለሮማ ቁልፍ ተጫዋች ነበር። የቀድሞው የሲቲ አጥቂ በዚህ የውድድር ዘመን በሊጉ 14 እንዲሁም በሻምፒዮንስ ሊጉ ደግሞ ስድስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። አሌክሳንደር ኮላሮቭና ፌዴሪኮ ፋዚዮም በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው።

ሮማ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሊቨርፑልን ሶስት ጊዜ ማሸነፍ ቢችልም እነዚህ ሁሉ ድሎች የተገኙት ግን በቅድመ ውድድር ዝግጅት የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ነበር።

ሮማ ባርሳን ከረታ ወዲህ ያደረጋቸውን ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ያልተሸነፈ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታት በአንዱ ከላዚዮ ጋር በአቻ ሲለያይ ጄኑዋን እና ስፓል ደግሞ ማሸነፍ ችለዋል።

ወቅታዊ ውጤቶች (በአጠቃላይ ውድድሮች)፡ ሽን፣ ሽን፣ ድል፣ አቻ፣ ድል፣ ድል

የቡድን ዜናዎች


ጆርዳን ሄንደርሰን ከሲቲ ጋር በተደረገው የመልስ ጨዋታ ያልተሰለፈ ቢሆንም፣ በዚህ ጨዋታ ጄምስ ሚልናር እና አሌክስ ኦክስሌድ-ቻምበርሌንን ያቀፈውን የሶስት ተጫዋቾች የመኃል አማካኝነት ሚናን እንደሚቀላቀል ግን ይጠበቃል።

ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ እና አንድሪው ሮበርትሰን በክለቡ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ አረፍት ከወሰዱ በኋላ በማክሰኞ ምሽቱ ጨዋታ ላይ ግን የመስመር ተከላካይነት ሚናቸውን መልሰው የሚያገኙ ይሆናል።

ክሎፕ ሳላህን፣ ሳዲዮ ማኔን እና ሮቤርቶ ፊርሚኖን ያቀፈውን የሶስት የፊት ተጫዋቾችን ሚና አሁንም እንደሚያስቀጥሉ ሲጠበቅ፣ ዦል ማቲፕ፣ ኤምሬ ቻን እና አዳም ላላና ግን በጉዳት ምክኒያት አሁንም ክለቡን ለረጅም ጊዜ የሚርቁ ተጫዋቾች ናቸው።

የእንግዳው ቡድን ሮማ 3-5-2 አሰላለፍ እንደሚመርጥ ሲጠበቅ፣ ኤዲን ጄኮ እና ፓትሪክ ሺክ ደሞ በአንፊልድ የሚደረገውን ጨዋታ በፊት በኩል የሚመሩ ተጫዋቾች ናቸው።

አሌሳንድሮ ፍሎሬንዚ እና ኮላሮቭ የክንፍ ተከላካይነት ሚናውን ሲወጡ፣ የመኃል አማካኝነት ሚናው ደግሞ ለዳኒኤል ደ ሮሲ፣ ኬቪን ስትሩትማን እና ራጃ ኒያንጎላን የተሰጠ ነው።

በሳምንቱ መጨረሻ ወደመጀመሪያ አሰላለፍ የተመለሰው ዲያጎ ፔሮቲ በዚህ ጨዋታም የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እንደሚካተት ይጠበቃል።

ግምታዊ አሰላለፎች


ሊቨርፑል፡ ካሪዩስ፣ አሌክሳንደር-አርኖልድ፣ ቫን ዳይክ፣ ሎቭረን፣ ሮበርትሰን፣ ሄንደርሰን፣ ሚልነር፣ ኦክስሌድ-ቻምበርሌን፣ ሳላህ፣ ፊርሚኖ፣ ማኔ

ሮማ፡ አሊሰን፣ ፋዚዮ፣ ማኖላስ፣ ኼሱስ፣ ፍሎሬንዜ፣ ስትሩትማን፣ ደ ሮሲ፣ ኒያንጎላን፣ ኮላሮቭ፣ ጄኮ፣ ሺክ

የእርስበእርስ ግንኙነት


ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በ2001-02 የውድድር ዘመን በሁለተኛው የማጣሪያ ጨዋታ ነበር። ሁለቱም ክለቦች በዚያ ዓመት ባርሴሎናን እና ጋላታሳራይን ገጥመዋል። ሊቨርፑል በመጀመሪያው ጨዋታ በሮም 0ለ0 አጠናቆ በመልሱ ጨዋታ በአንፊልድ 2ለ0 ማሸነፍ ችሏል።

በአውሮፓውያኑ ውድድር ላይ ሁለቱ ክለቦች በታሪካቸው ለአምስት ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን ሊቨርፑል ሁለቱን ሲያሸንፍ፣ አንዱን ሮማ አሸንፏል። በሁለቱ ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

ሮማ ሊቨርፑልን በአውሮፓ መድረክ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ማሸነፍ የቻለው በ2000-01 በዩሮፓ ካፕ አራተኛ ዙር ላይ 1ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ነበር። ይሁን እንጂ ሊቨርፑል በመልሱ ጨዋታ 2ለ0 አሸንፎ ወደቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል።

Advertisements