ኦሊቨር በማንችስተርና ቼልሲ መካከል የሚደረገውን የኤፍኤ ዋንጫ ፍፃሜ ሊዳኙ ነው

በቅርቡ በጁቬንቱስና በሪያል ማድሪድ መካከል የተደረገውን የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ በመዳኘት በጨዋታው የጭማሪ ሰዓት ለማድሪድ በሰጡት አወዛጋቢ የፍፁም ቅጣት ምት የሚታወሱት ማይክል ኦሊቨር የፊታችን ግንቦት 11፣ 2010 ዓ.ም በማንችስተር ዩናይትድና በቼልሲ መካከል የሚደረገውን የኤፍኤ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ለመዳኘት ተመርጠዋል።

የ33 ዓመቱ ዳኛ በሊ ቤትስ እና ኢያን ሁሴን ረዳት ዳኝነት ታግዘው ይህን የዌምብሌይ የፍፃሜ ጨዋታ የሚዳኙም ይሆናል።

ኦሊቨር ለዳኝነቱ መመረጣቸውን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “የስልክ ጥሪው ሲደርሰኝ ኩራት እና ክብር ተሰምቶኛል።” በማለት ገልፀዋል።

ኦሊቨር አክለውም “ነገሮች ያስቃሉ። ምክኒያቱም በ1994 በማንችስተር ዩናይትድና ቼልሲ ማካከል የተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትኩት ጨዋታ እንደሆነ አስታውሳለሁ። አሁን ደግሞ ከ24 ዓመታት በኋላ በሁለቱ ክለቦች መካከል የሚደረገውን የኤፍኤ ዋንጫ ፍፃሜ የመዳኘት ኃላፊነት አግኝቻለሁ።” በማለት ተናግረዋል።

በዚህ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነቱን ሚና ደግሞ ኒክ ስዋርብሪክ በሚል ማክዶኖፍ ታግዘው የሚወጡ እንደሆነም ታውቋል።