ስንብት / አንድሬስ ኢኒየስታ በውድድር አመቱ መጨረሻ ከባርሴሎና ጋር እንደሚለያይ አሳወቀ

የካታላኑ ጥበበኛ ተጫዋች አንድሬስ ኢንየስታ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫው ከባርሴሎና ጋር ከ 21 አመት ቆይታ በኋላ በውድድር አመቱ መጨረሻ እንደሚለያይ በእንባ ገልፅዋል።

በውጤት ያሸበረቁ አመታትን ከባርሴሎና ጋር ያሳለፈው ኢኒየስታ በመጨረሻም ቀደም ብለው ባለፉት አመታት ከክለቡ እንደተለዩት ኮከቦች ሁሉ በአመቱ መጨረሻ ከባርሴሎና ጋር እንደሚለያይ አሳውቋል።

ተጫዋቹ ከልጅነቱ ጀምሮ የቆየበትን ክለቡን እንደሚለያይ በቡድን ጓደኞቹ ፊት ሲያሳውቅ ስሜታዊነት የታየበት ሲሆን አይኑም በእንባ ተሞልቶ ታይቷል።

ኢኒየስታ በ 15 አመቱ

ኢኒየስታ በድል የታጀበ ቆይታው አራት የቻምፕየንስ ሊግ እና ስምንት የላሊጋን ዋንጫ ያሸነፈ ሲሆን በአጠቃላይ 31 ዋንጫዎችን አግኝቷል።

እሁድ ባርሴሎና የላሊጋ ዋንጫን ማንሳቱን ካረጋገጠ ደግሞ ኢኒየስታ በጠቅላላው ያነሳው የዋንጫ ብዛት ወደ 32 የሚያሳድግ ይሆናል።

“ይህ አመት ለኔ የመጨረሻዬ ነው።የቡድን ጓደኞቼን አመሰግናለው።በዚህ ክለብ ብቸኛ አላማዬ ውጤታማ መሆን ነበር ያንን ጊዜም አሳክቻለው።”ሲል ተናግሯል።

ኢኒየስታ እና ኩቲንሆ – ከስንብት መግለጫው በፊት

ወደ ቻይና እንደሚያመራ የሚጠበቀው ኢኒየስታ በመረጃው ዝምታ ቢመርጥም በአውሮፓ ግን መጫወት እንደማይፈልግ አረጋግጧል።

“አሁንም መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች አሉ።ነገርግን ባርሴሎናን በተቃራኒ ሆኜ መግጠም ስለማልፈልግ በአውሮፓ አልጫወትም።” ሲል ጨምሮ ተናግሯል።

በእግርኳስ ከታዩት ምርጥ አማካዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ኢኒየስታ ሀገሩ ስፔን በ 2010 የአለም ዋንጫ ላይ አሸናፊ እንድትሆን ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

የማሸነፊያዋን ጎል ሆላንድ ላይ ያስቆጠረው ኢኒየስታ በዛኑ አመት የባሎንዶር አሸናፊ መሆን እንደሚገባው በስፋት ቢነገርም ሳይሳካለት ቀርቷል።

በዚሁ ሳምንትም የፈረንሳዩ መፅሄት ፍራንስ ፉትቦል በይፋ ተጫዋቹን 2010 ላይ የባሎንዶር ሽልማት ባለመሸለሙ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል።

Advertisements