ስንብት / ኡናይ ኤምሬ በቀጣይ የውድድር አመት የፒ ኤስ ጂ አሰልጣኝ ሆነው እንደማይቀጥሉ አሳወቁ

ለሁለት አመታት የፓሪሱን ክለብ ያሰለጠኑት ስፔናዊው ኡናይ ኤምሬ ከውድድር አመቱ በኋላ ከሀላፊነታቸው እንደሚለቁ ይፋ አድርገዋል።

<!–more–>

ስፔናዊው አሰልጣኝ የፔዤ አሰልጣኝ ሆነው ከተቀጠሩ በኋላ ዘንድሮ የፈረንሳይ ሊግ ኣ ዋንጫን ማንሳት የቻሉ ሲሆን የፈረንሳይ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይም መቅረብ ችለዋል።

በመጀመሪያ አመታቸው በሞናኮ ተቀድመው ዋንጫውን ያጡ ሲሆን በቻምፕየንስ ሊጉም በባርሴሎና ተሸንፈው ከውድድሩ መውጣታቸው ይታወሳል።

አሰልጣኙ በተለይ በአውሮፓ መድረክ አሸናፊ ለመሆን የአለም የዝውውር ሪከርድ በመስበር ጭምር ብዙ ብር አውጥተው የተለያዩ ተጫዋቾችን ቢያዛወወሩም ሊሳካላቸው ግን አልቻለም።

ይህም የክለቡ ባለቤቶች እና ደጋፊዎችን ያላስደሰተ ሲሆን አሰልጣኙም ክለቡን በአውሮፓ ለማንገስ ባለመቻላቸው ከውድድር አመቱ መጨረሻ በኋላ ከክለቡ ጋር እንደሚለያዩ እራሳቸው አሳውቀዋል።

ነገርግን አሰልጣኙ ውሳኔውን ያሳለፉት በራሳቸው ፍላጎት መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ በማሳወቅ የግንቦት 8 ቱ የፈረንሳይ ዋንጫ ጨዋታ የመጨረሻቸው እንደሚሆን ግልፅ አድርገዋል።

46 አመታቸው ላይ የሚገኙት ኤምሬ “ከክለቡ ጋር እንደምለያይ ለተጫዋቾቹ እና ለፕሬዝዳንቱ ነግሪያቸዋለው።ሁሉንም አመሰግናለው፣አሁን የሚቀረው የፈረንሳይ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ነው።”በማለት ስንብታቸውን አውጀዋል።

ፔዤ ማንን በአሰልጣኝነት ሊቀጥር ይችላል የሚለው ቀጣዩ ጥያቄ ሲሆን የቀድሞው የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ የነበሩት ቶማስ ቱኸል ቡድኑን የማሰልጠን እድል እንዳላቸው በስፋት እየተነገ ይገኛል።

ከ 22 አመታት በኋላ ከመድፈኞቹ ጋር አንደሚለያዩ ያሳወቁት አርሰን ዌንገር እንዲሁ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው አዲሱ የፔዤ አሰልጣኝ ሊሆኑ ከሚችሉ የአሰልጣኞች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።

ልዊ ቫንሀልም ከትናንት በስትያ በሰጡት አስተያየት መሰረት ከአንድ ክለብ የቀረበላቸው ጥያቄ እምቢ የሚሉት እንዳልሆነ ከተናገሩ በኋላ ምናልባትም ጥያቄ ያቀረበላቸው ከፔዤ ሊሆን እንደሚችል ተጠርጥሯል።

ልዊስ ኤነሪኬም ሌላኛው በእጩ ዝርዝር ውስጥ ስሙ የሰፈረ አሰልጣኝ ቢሆንም የክለቡ ምርጫ ግን በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

Advertisements