የሰንደርላንድ ባለቤት ክለቡን ለመሸጥ ተስማሙ፤ አሰልጣኙንም አሰናበቱ

ወደ እንግሊዝ ሶስተኛ ዲቪዝዮን የሆነው ሊግ አንድ መውረዱን ያረጋገጠው ሰንደርላንድ የክለቡን አሰልጣኝ ክሪስ ኮልማንን ማሰናበቱን ካሳወቀ ከ 30 ደቂቃ በኋላ የክለቡ ባለቤት ቡድኑን ለመሸጥ እንደተስማሙ አሳወቁ።

የቀድሞ የዌልስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ክሪስ ኮልማን ከሰንደርላንድ ጋር ለአምስት ወራት ቆይታ ካደረጉ በኋላ ከሀላፊነታቸው ተነስተዋል።

አሰልጣኙ ወደ ሰንደርላንድ ካቀኑ በኋላ ቡድኑን የማትረፍ ሀላፊነት ተቀብለው ስራቸውን ቢጀምሩም ሳይሳካላቸው ሰንደርላንድ ወደ ሊግ አንድ መውረዱ እርግጥ ሆኗል።

ኮልማን ህዳር ወር ላይ ሲሞን ግራይሰንን ተክተው ወደ ስታድየም ኦፍ ላይት ቢያቀኑም ከ 29 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት አምስት ጨዋታዎችን ሲሆን በ 16 ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ሽንፈትን አስተናግደዋል።

ክለቡ በመግለጫው”ክሪስ ኮልማን እና ረዳታቸው ኪት ሲሞንስ ከኮንትራታቸው ነፃ እንዲሆኑ ተደርገዋል።ክለቡ አስከፊ በነበረው አመት ላይ ላደረጋችሁት ጥረት ምስጋናውን ያቀርባል፣ከዚህ በላይ ተጨማሪ አስተያየት ክለቡ መስጠት አይችልም።”በማለት ከአሰልጣኞቹ ጋር መለያየቱን አሳውቋል።

የክለቡ ባለቤት ኢሊስ ሾርትም ክሪስ ኮልማን መሰናበታቸው ከተረጋገጠ ከ 30 ደቂቃ በኋላ ክለቡን ለመሸጥ ስምምነት ላይ እንደደረሱ አሳውቀዋል።

ስምምነቱ ሁሉ የተጠናቀቀ ሲሆን የስም ዝውውሩንም ለመረጨረስ ከእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ማረጋገጫ ብቻ ማግኘት ይጠብቃቸዋል።

ኢሊስ ሾርት በመግለጫቸው እስከ አሁን ክለቡን ለመሸጥ ሲሞክሩ እንደቆዩ አሁን ግን ትክክለኛውን ክለቡን የሚገዛ ግሩፕ ማግኘታቸውን አሳውቀዋል።

ክለቡን የሚገዛው ደግሞ በናሽናል ሊግ የሚሳተፈው የኢስትሊህ ግሩፕ ሊቀመንበር የሆኑት ስቲዋርድ ዶናልድ እንደሆኑ ታውቋል።

Advertisements