ካቫኒ በፒኤስጂ ደስተኛ መሆኑን ገለፀ

ኤዲንሰን ካቫኒ ፒኤስጂን ለመልቀቅ የማይጣደፍ ሲሆን፣ ወደፊትም በክለቡ እንደሚቆይ ይጠበቃል።

ኡራጓዊው ተጫዋች ናፖሊን በ2013 ከለቀቀበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም ውድድሮች ላይ የክለቡ የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ አስቆጠሪ በመሆን በፈረንሳይ ድንቅ የሆነ የጨዋታ ዘመን ማሳለፍ ችሏል።

በግሉም ባለፈው የውድድር ዘመን ለኤዲሰን ካቫኒ የእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመን በተለየ ሁኔታ ምርጥ የሚባል ነበር። ተጫዋቹ በ36 የሊግ 1 ጨዋታዎች 35 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ነገር ግን በውድድር ዘመኑ ፒኤስጂ ሞናኮን በልጦ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ሳይቻለው ቀርቷል።

ሶስት ጨዋታዎች በቀሩት በዚህ የውድድር ዘመንም ባደረጋቸው 27 ጨዋታዎች ወዳለፈው የውድድር ዘመን የግብ ቁጥር የተቃረበ ግብ (29) ማስቆጠር ችሏል። ይሁን እንጂ እነዚህ ግቦቹ ፒኤስጂን እንደአምናው ሁሉ መና ቢስ ያደረጉት ሳይሆን በአንፃሩ የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ተደላድሎ እንዲቀመጥ ያደረጉ ሆነዋል።

ምንም እንኳ በፓሪስ ለእንድ የውድድር ዘመን ብቻ ቆይታ ያደረገው ኔይማር ክለቡን እንደሚለቅ ስሙ ከዝውውር ጋር ቢያያዝም ኤዲሰን ካቫኒ ግን በክለቡ በመቆየት ተጨማሪ የዋንጫ ክብሮችን የማሳካት ከፍተኛ ፍላጎት አለው።

“ከፓሪስ ጋር ኮንትራት አለኝ።” ሲል ካቫኒ ለፈረንሳዩ ካናል ፕለስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግሮ “በእዚህ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነኝ።

“አንዳንድ ጊዜ ነገሩ በተጫዋቹ ላይ ብቻ አይመሰረትም። በክለቡ ውስጣዊ ጉዳዮችም ጭምር እንጂ።

“በእዚህ ደስተኛ ነኝ። በዚህ ቡድንና መለያ አሸናፊነቴን እንደምቀጥል ተስፋ አለኝ።” ብሏል ከቫኒ።

ካቫኒ ፒኤስጂ በሳምንቱ መጨረሻ ቀን ከጊዩንጋምፕ ጋር አቻ መለያየት የቻለባቸውን ሁለት ግቦች በማስቆጠር በዝላታን ኢብራሂሞቪች ተይዞ የነበረውን የክለቡን የሊግ 1 ውድድር ከፍተኛ ግብ አስቆጠሪነት ሪከርድ መጋራት ችሏል።