ጉዳት ላይ የሚገኘው ሮበን ከሪያል ማድሪድ ጋር ከሚደረገው ጨዋታ ውጪ ሆነ

ሆላንዳዊው ተጫዋች አሪየን ሮበን ጭኑ ላይ በገጠመው የጡንቻ ጉዳት ምክኒያት በሻምፒዮንስ ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ማክሰኞ ምሽት ወደሪያል ማድሪድ አምርቶ ከሚጫወተው የባየር ሙኒክ ቡድን ስብስብ ውጪ ሆኗል።

ሮበን ባለፈው ሳምንት በተደረገው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ገና በስምንተኛው ደቂቃ በገጠመው ጉዳት ሜዳ ለቆ ለመውጣት ተገዶ ነበር። በሳምንቱ መጨረሻ ባየር ሙኒክ ኢንትራክት ፍራንክፈርትን 4ለ1 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይም መስለፍ አልቻለም።

ሆላንዳዊው ተጫዋች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ልምምድ መስራት ችሎ የነበረ ቢሆንም፣ ለማክሰኞው ጨዋታ መድረስ ግን አለመቻሉ ታውቋል።

ዛሬ (ሰኞ) ስም ዝርዝራቸው ይፋ በሆነው የባየር ሙኒክ የተጫዋቾች ስብስብ ውስጥም የሮበን ስም አልተካተተም።

ይሁን እንጂ ጉዳት የነበረባቸው ኻቪ ማርቲኔዝ እና ዴቪድ አላባ ከቡድኑ ጋር አበረው የሚጓዙ ተጫዋቾች ሆነዋል።

ባየር ባለፈው ሳምንት በመጀመሪያው ጨዋታ በሜዳው በሪያል ማድሪድ 2ለ1 መሸነፉ ይታወሳል።

Advertisements