ሞ ሳላህ ከግብፅ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ቅራኔ ውስጥ እንደገባ ተገለፀ

ግብፃዊው ሞ ሳላህ በግብፅ እግርኳስ ማህበር ተግባር ቅራኔ ውስጥ እንደገባ ታውቋል

አመቱን በስኬት ለማጠናቀቅ የተቃረበው ሞ ሳላህ በሊቨርፑል እያሳየ ያለው አቋሙ ከየአቅጣጫው ትኩረትን መሳብ ችሏል።

በፕሪምየርሊጉም ይሁን በቻምፕየንስ ሊጉ ላይ አስገራሚ አቋሙን ማሳየቱን የቀጠለ ሲሆን ቡድኑንም ከ 10 አመት በኋላ በቻምፕየንስ ሊጉ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ለማብቃት ጫፍ ላይ ይገኛል።

ሀገሩን ግብፅንም ለ2018 የአለም ዋንጫ ተሳትፎ በማብቃት የአምበሳውን ድርሻ መውሰድ ችሏል።

ተጫዋቹ እያሳየ ያለው ስኬታማ ጉዞ ለባሎንዶር ተፎካካሪ እንደሚያደርገውም የሚናገሩ እየበዙ መጥተዋል።

ሞ ሳላህ እውቅናው እየገነነ ሲመጣም በምስል መብቱ ላይ ማስታወቂያ ለመስራት ከቮዳፎን ጋር ስምምነት ፈፅሟል።

ነገርግን የግብፅ እግርኳስ ፌዴሬሽን ወደ ራሺያ በሚያቀናው ይፋዊ የብሔራዊ ቡድኑ አውሮፕላን ላይ የተጫዋቹን ምስል ካደረገ በኋላ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሳላህን ቅር አሰኝቷል።

ሳላህ ከሌላ ተቋም ጋር በምስል መብቱ ላይ ስምምነት መፈፀሙን ተከትሎ የግብፅ እግርኳስ ማህበር ባደረገው ተግባር ደስተኛ አላደረገውም።

“የሆነው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው።ተቀራርበን ብንነጋገር ኖሮ የተሻለ ነበር።” ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል።

የተጫዋቹ ወኪል ሬሚ አባስ በበኩሉ “እስካሁን ድረስ መፍትሄ ለመፍጠር ቀርቦ ያናገረን የለም።ሁሉም ዝም ነው ያለው።በዚህ አይነት ያለ እኛ ፈቃድ ብዙ ማስታወቂያዎችን እናያለን።ለማንኛውም የሚሆነውን እንመለከታለን።” ብሏል።

“የግብፅ የወጣቶች እና የስፖርት ሚኒስቴር የሆኑት ካልድ አብዲላዚዝ እንዳሉት ከሆነ ከግብፅ እግርኳስ ማህበር ጋር የሞ ሳላህን ጥያቄ ለመመለስ ስምምነት ላይ ደርሰናል።”ሲሉ ተናግረዋል።