ሮቤርቶ ማንቺኒ የአዙሪዎቹ አሰልጣኝ ለመሆን ንግግር እንደጀመሩ ተነገረ


2011/2012 ላይ ድራማዊ በሆነ መንገድ የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ዋንጫ ያሸነፉት ሮቤርቶ ማንቺኒ አዲሱ የጣሊያን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመሆን ድርድር ጀምረዋል።

53ኛ አመታቸው ላይ የሚገኙት ማንቺኒ በላዚዮ፣በፊዮረንቲና እና በኢንተር ሚላን ማሰልጠን የቻሉ ሲሆን ወደ እንግሊዝም አቅንተው ማን ሲቲን ውጤታማ አድርገዋል።

ወደ ቱርክ አቅንተው ጋላታሳርይን ማሰልጠን የቻሉት ማንቺኒ ከ2017 በኋላ የራሺያውን ዜኒት ፒተርስበርግን እያሰለጠኑ የሚገኙ ሲሆን አቡን ደግሞ ሀገራቸውን ጣሊያን ለማሰልጠን እድሉ እንደተፈጠረላቸው ታውቋል።

ስካይ ኢታሊያን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ የመገናኛ ብዙሀን ዛሬ ይዘውት በወጡት መረጃዎች መሰረት አሰልጣኙ ከእግርኳስ ማህበሩ ኮሚሺነር አሌሳንድሮ ኮስታኩርታ እና ከቡድኑ ዳይሬክተር ጋብርኤል ኦሪያሊ ጋር በሮም ተገናኝተው ውይይት አድርገው ስምምነት ላይ እንደደረሱ ታውቋል።

በስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይም ለመወያየት የራሺያ ፕሪምየርሊግ ሲጠናቀቅ በፈረንጆቹ ግንቦት 13 ላይ ቀጠሮ እንደያዙ ታውቋል።

ማንቺኒ ስምምነቱ በመልካም ሁኔታ ከተጠናቀቀ ጂያን ፒሮ ቬንቹራን ተክተው በይፋ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆነው ይሾማሉ።

በሀላፊነታቸውም ለ 2020 የአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያዎች ላይ አዙሪዎቹን ማዘጋጀት ቅድሚያ ስራቸው ይሆናል።

ጣሊያን ከ 2018 የአለም ዋንጫ የጥሎማለፍ ማጣሪያ በሰዊድን ተሸንፎ ከውድድሩ ተሳትፎ ውጪ ከሆነ በኋላ ከ 21 አመት በታች አሰልጣኙ ሉዊጂ ዲ ባጂዮ እየሰለጠነች መቆየቷ ይታወሳል።

Advertisements