የሊቨርፑሉ ምክትል አሰልጣኝ አርሰናልን በዋና አሰልጣኝነት ሊረከቡ ነው

የሊቨርፑሉ ምክትል አሰልጣኝ ዜልይኮ ቡቫች ሰኞ ዕለት ሊቨርፑልን እንደሚለቁ በተዘገበ የአንድ ቀን ልዩነት አርሰን ቬንገርን ተክተው አርሰናልን በዋና አሰልጣኝነት ሊይዙ እንደሆነ ከቦስኒያ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

በ2015 የርገን ክሎፕ ዜሊይኮ ቡቫችን ከዶርትሙንድ ወደሊቨርፑል ሊያመጡ እንደሆነ የዘገበው የቦስኒያ የስፖርት የህትመት ሚዲያ የሆነው ፕራቭዳ ቢኤል አሰልጣኙ ወደእንግሊዝ ለንደን ለማምራት ሁሉ ነገር እንደተመቻቸላቸው ዘግቧል።

ሌሎች ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ደግሞ አርሰናል እንደአሌግሪ፣ ኢነሪኬ እና ካርሎ አንቸሎቲ ያሉ አሰልጠኞችን ለማስፈረም ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ነው።

በመሆኑም ክለቡ እነዚህን አሰልጣኞች ለመቅጠር ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ላለማድረግ ሲል ለረጅም ጊዜያት ከየርገን ክሎፕ ጋር መስራት የቻሉትን እና ቀኝ እጃቸው የሆኑትን ዜሊይኮ ቡቫችን ሊቀጥር ይችላል።

ከየርገን ክሎፕ ጋር ለ17 ዓመታት ያህል አብረው መስራት የቻሉት ቡቫች ለክሎፕ የአሰልጣኞች ቡድን የታክቲክ ምጡቅነት እንደልዩ ባለ”አዕምሮ” ሰው ይቆጠራሉ።

ምንም እንኳ ሊቨርፑል አሰልጣኙ ለሻምፒዮን ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ወደሮም ከተጓዘው የቀዮቹ ቡድን ስብስብ ጋር አብረው ያልተጓዙት ቦቫች በግላዊ ጉዳዮ ምክኒያት እንጂ ክለቡን በቋሚነት ሊለቁ ነው ከሚለው ዘገባ ጋር በተያያዘ አለመሆኑን ይግለፅ እንጂ ዛሬ ከሰርቢያ የወጣው መረጃ ግን አሰልጣኙ መድፈኞቹን በዋና አሰልጣኝነት ለመረከብ ዝግጅት ለማድረግ ሲሉ እንደሆነ ገልፅዋል።

ይህ የዝውውር የወሬ ጭምጭምታ እውነት ከሆነም ቦቫች የየርገን ክሎፑን በክፍተኛ ኃይል ተጭኖ የመጫወት ታክቲክ በሰሜን ለንደኑ ክለብም ተግባራዊ እንደሚያደረጉት ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

Advertisements