ሮማ ከ ሊቨርፑል | የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ

ሊቨርፑል በመጀመሪያው ጨዋታ ያገኘውን የሶስት ግቦች ልዩነት ስንቅ አድርጎ በቻምፒዮንስ ሊጉ ፍፃሜ ከሪያል ማድሪድ ጋር የመፋለም ተስፈን ሰንቆ በግማሽ ፍፃሜው የመልስ ጨዋታ ሮማን ለመግጠም ወደጣሊያኗ መዲና አምርቷል።

የየርገን ክሎፑ ቡድን በመጀመሪያው ጨዋታ ጂያሎሮሲዎቹን በአንፊልድ በአምስት ግቦች ልዩነት መምራት ችሎ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ሰዓት የተቆጠሩበት ሁለት ግቦች ለሮማ መልሶ የመፋለም ተስፋን የሰጡ ሆነዋል።

ሮማ በሩብ ፍፃሜው የመልስ ጨዋታ በባርሴሎና ላይ የፈፀመው የ3ለ0 ድል እና ለግማሽ ፍፃሜው እንዲበቃ ያደረገው ገድል በእንግሊዝ የደረሰበትን የ5ለ2 ሽንፈት ዳግመኛ በመቀልበስ እንደሚደግም ይጠበቃል።

የሚጠበቅበትን ተጋድሎ ፈፅሞ ይህን ጨዋታ የሚወጣ ክለብ ደግሞ በደርሶ መልስ ጨዋታ 4ለ3 በሆነ ውጤት ለፍፃሜ ከበቃው የዚነዲን ዚዳኑ ሪያል ማድሪድ ጋር በፍፃሜው የሚፋለም ይሆናል።

ጨዋታው መቼ ይደረጋል?

ሮና በጣሊያኗ ዋና ከተማ ሮም በሚገኘው ስታዲዮ ኦሊምፒኮ ረቡዕ ምሽት 3፡45 ላይ ሊቨርፑልን ያስተናግዳል።

ጨዋታውን በቀጥታ እንዴት መመልከት ይቻላል?

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች በአፍሪካ ሱፐርስፖርት 3፣ በሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ቤንስፖርት 11 እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ቢቲ ስፖርት 2 የቴሌቪዥን ቻናሎች ይህን ጨዋታ በቀጥታ መመልከት ይቻላል።

ስለቡድኖቹ ምን ዕይነት ዜናዎች አሉ?

ሮማ

አማካኙ ዲያጎ ፔሮቲ (በቁርጭምጭሚቱ ላይ) እና ኬቪም ስትሩትማን (በጎድን አጥንቱ ላይ) በመጀመሪያው ጨዋታ በገጠማቸው ጉዳት በዚህ ጨዋታ ላይ መሰለፋቸው አጠራጣሪ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው። ተከላካዩ ሪክ ካርዶርፕ እና አጥቂው ግሪጎይር ዳፍረል ደግሞ ሙሉ በሙሉ በዚህ ጨዋታ ላይ አለመሰለፋቸው እርግጥ የሆኑ ተጫዋቾች ናቸው፡

እንዲሁም በአንፊልዱ ጨዋታ አጋማሽ ላይ ጉዳት ገጥሟቸው ሜዳ ለቀው ለመውጠት ተገደው የነበሩት ስትሩትማን እና ሴንጊዝ እንዲሁም በሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታ የሮማን ግቦች ማስቆጠር የቻሉት ስቴፋን ኤልሻራውይ እና ፓትሪክ ሺክ በዛሬ ምሽቱ ጨዋታ ላይ እንደሚመለሱ የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

ሊቨርፑል

ክሎፕ ሮማን በሚገጥሙበት የሻምፒዮንስ ሊጉ የግማች ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ የመጀመሪያ ተመራጭ የተከላካይ ክፍላቸውን የመጀመሪያ ተሰላፊ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በዚሁ መሰረት ደዣን ሎቭረንና አንድሪው ሮበርትሰን ወደመጀመሪያ ተሰላፊነት ለመምጣት ዝግጁ ሲሆኑ፣ ጆ ጎሜዝ በገጠመው ጉዳት ምክኒያት ከቡድኑ ጋር ያለተጓዘ በመሆኑ ትሬንት አሌክሰንደር-አርኖልድ በሚገባ ሊወጣው ወደሚችልበት የቀኝ መስመር ተከላካይነት ሚናው ይመለሳል። ራግነር ክላቫን እና አልቤርቶ ሞሬኖ ዳግሞ በቅዳሜው ግብ አልባ ጨዋታ ላይ በመጫወታቸው በዚህ ጨዋታ ላይ የመሰለፍ ዕድላቸው ዝቅ ያለ ነው።

ክሎፕ በአማካኝ ስፍራቸው ላይ በምቾት የተለመዱት አማካኛቻቸውን መጠቀም የማይችሉ በመሆናቸው ከጉዳት የተረፏቸውን ሶስቱን ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች፣ ጆርዳን ሄንደርሰን፣ ጄምስ ሚልናር እና ጆርጂኒዮ ዊይናልደምን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ለማካተት ይገደዳሉ።

ምን አይነት የመጀመሪያ አሰላለፎች ይጠበቃሉ?

ሊቨርፑል (4-3-3): ካሪዩስ፣ አሌክሳንደር-አርኖልድ፣ ሎቭረን፣ ቫን ዳይክ፣ ሮበርትሰን፣ ሚልነር፣ ሄንደርሰን፣ ዊይናልደም፣ ሳላህ፣ ፊርሚኖ፣ ማኔ

ሮማ (3-5-2): አሊሰን፣ ፋዚዮ፣ ማኖላስ፣ ኹዋን ኼሱስ፣ ፍሎሬንዜ፣ ስትሩትማን፣ ደ ሮሲ፣ ኒያንጎላን፣ ኮላሮቭ፣ ሺክ፣ ጄኮ

ስለጨዋታው ምን ተባለ?

የሊቨርፑሉ ተከላካይ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ የሮማውን ስታዲዮ ኦሎምፒኮ የተቀናቃኝነት መንፈስ አስመልክቶ የሚከተለውን ተናግሯል።

“ልንፈፅመው የሚገባንን ስራ ይዘን ለማሸነፍ ወደዚያ እያመራን እንገኛለን። ቀላል የማይባል ድባብ እና የእኛ ደጋፊዎች በእነሱ ላይ ያደረጉት አይነት ድባብ እንደሚጠብቀን ማወቃችንም ቢሆን ግልፅ ነው።

“በአዕምሮ እና በአካል ዝግጁ መሆን አለብን። ለእንደእዚህ አይነቱ ጨዋታ እና ለእንደዚህ ዓይነቱ ዕድል ህይወትህን ሙሉ ለአመታት ልምምድ ታደርጋለህ። እኔም ረቡዕ ምሽት ለማደርገው አይነት ጨዋታ እስካሁን ራሴን ሳዘጋጅ ቆይቻለሁ።”

ሮማ በሩብ ፍፃሜ በባርሴሎና ላይ የፈፀመውን ውጤት የመቀልበስ ጅብዱ አሁንም እንደሚደግሙት አሰልጣኙ ኢዩሴቢዮ ዲ ፍራንሲስኮ ያምናሉ።

“ዳግመኛ የማገገም ብቃት እንዳለን አሳይተናል። አሁንም ያንን ዳግመኛ ማድረግ እንደሚኖርብን እምነቱ አለን። እኔ እምናለሁ። የእኔ ማፈክርም ይኸው ነው። ወደተጫዋቾቼ ላጋባባቸው የምፈልገውም ይሄንኑ ነው።”

የሮማው አማካኝ ራጃ ኒያንጎላ ሮማ ረቡዕ ምሽት ሊወጣው የሚግባ የቤት ስራ እንዳበት በሚገባ ተገንዝቧል።

“ሁላችንም አስቸጋሪ መሆኑን በሚገባ የምናውቅ ይመስለኛል። ነገር ግን ከባርሴሎና ጋር ያደረግነውም አስቸጋሪ ነበር። ማድረግ በምንችለው ነገር ላይ እምነት ሊያድርብን ይገባል። በቃ ይኸው ነው።

“ከባርሳሎና ጋር ካደረግነው አንፃር ይህ ይበልጥ አስቸጋሪ የሚሆን ይመስለኛል። ምክኒያቱም ይህኛው በአካል ብቃቱ በኩል የተሻለ ቡድን ነው።

“የሊቨርፑል ተጫዋቾች [ከመጀመሪያው ጨዋታ] በበለጠ ወጥ ብቃት ሊያሳዩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለኝ።

“በመጨረሻ ሰዓት ሁለት ግቦችን አስቆጥረናል። ያ ደግሞ የተስፋ ጭላንጭል ፈጥሮልናል። እናም አሁንም ህያው ነን። አሁን ግን ያን ስህተት መድገም አንችልም።”

Advertisements