አትሌቲኮ ማድሪድ ከ አርሰናል | የዩሮፓ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ

አርሰናል የአርሰን ቬንገር የአሰልጣኝነት ዘመን በመልካም ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይቻለው ዘንድ በዩሮፓ ሊግ የሚያደርገው ይህ ጨዋታ የሞት ሽረት ትግል ይሆንበታል

በመጀመሪያው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የአብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ በጎዶሎ ተጨዋች የተጫወተው አትሌቲኮ ማድሪድን ማሸነፍ ሳይችል 1ለ1 በሆነ ውጤት ያጥናቀቀው የሰሜን ለንደኑ ክለብ ፍፃሜውን ለመቀላቀል በ12 ተከታታይ ጨዋታዎች በሜዳው ዋንዳ ሜትሮፓሊታኖ ሽንፈት ያልደረሰበትን የስፔኑን ክለብ ያለመሸነፍ ጉዞ መግታት የሚችል የመጀመሪያው ክለብ መሆን ይጠበቅበታል።

ጨዋታው መቼ ይደረጋል?

አትሌቲኮ ማድሪድ አርሰናልን የሚገጥምበት ይህ የዩሮፓ ሊፍ የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ሀሙስ ሚያዝያ 25 ምሽት 4፡05 ላይ በማድሪዱ ዋንዳ ሜትሮፓሊታኖ ስታዲየም የሚደረግ ነው።

ጨዋታውን እንዴት በቀጥታ መመልከት ይቻላል?

ይህ ጨዋታ ከሰሃራ በታች በአፍሪካ (ኢትዮጵያን ጨምሮ) በሱፐር ስፖርት 3፣ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ቤንስፖርት 11 እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም በቢቲ ስፖርት 2 የቴሌቪዥን ቻናሎች በቀጥታ ይተላለፋል።

የከዚህ ቀደም የእርስ በርስ ግንኙነታቸው ምን ይመስላል?

አርሰናልና አትሌቲኮ ማድሪድ ባለፈው ሳምንት 1ለ1 በሆነ ውጤት ከተለያዩበት የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ውጪ በአውሮፓ አበይት ውድድሮች ላይ ፈፅሞ ተገናኝተው አያውቁም። ይሁን እንጂ በ2009 የቅድመ ውድድር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አርሰናል በኤመራትስ ዋንጫ ላይ አትሌቲኮን 2ለ1 ማሸነፍ ችሎ ያውቃል።

ቡድኖቹን የተመለከቱ ምን አይነት ዜናዎች አሉ?

አርሰናል

አርሰናል ምንም አይነት አዲስ የሆነ አሳሳቢ ጉዳት የለበትም። ይልቁንስ መድፈኞቹ በመጀመሪያው ጨዋታ በጉዳት ምክኒያት ሳያሰልፉት ቀርተው የነበረውን ሄነሪክ ሚክሂታሪያንን ይዘው ወደስፔን ተጉዘዋል።

በሳምንቱ መጨረሻ በማንችስተር ዩናይትድ ሽንፈት በገጠማቸው ጨዋታ ቀላል የሚባል ጉዳት ገጥሞት የነበረው አሌክሲ ኢዎቢም ከቡድኑ ጋር አብሮ ተጉዟል። ከዚህ ውጪ በዚህ ጨዋታ ላይ መሰለፍ የማይችለው ፒየር ኤመሪክ-ኦውባምያንግ እንዲሁም የጉልበት ጉዳት ያለበትና ከተረከዝ ጉዳቱ እስከሁን ያላገገመው ሳንቲ ካዘሮላ አሁንም በዚህ ጨዋታ ላይ የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።

በግብ ጠባቂነቱ ሚና ከቋሚ ተሰላፊው ፒተር ቼክ ይልቅ ዴቪድ ኦስፒና የመጀመሪያ ተሰላፊ እንደሚሆንም ቬንገር ገልፀዋል።

አትሌቲኮ ማድሪድ

ዲያጎ ኮስታ በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሳምንቱ መጨረሻ የመጀመሪያ ተሰላፊ መሆን ችሏል። በመሆኑም የቀድሞው የቼልሲ አጥቂ በዚህ ጨዋታ ላይ የመጀመሪያ ተሳላፊ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሲሜ ቭራስሂልኮ ባለፈው ሳምንት በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክኒያት በዚህ ጨዋታ ላይ የማይሰለፍ ብቸኛው የአትሌቲ ተጫዋች ነው።

ምን አይነት ግምታዊ አሰላለፎች ይጠበቃሉ?

አትሌቲኮ ማድሪድ (4-4-2): ኦብላክ፣ ኹዋንፍራን፣ ጎዲን፣ ጊሜኔዝ፣ ሉካስ፣ ኮሬያ፣ ሳኡል፣ ፓርቴ፣ ኮኬ፣ ኮስታ፣ ግሪዝማን

አርሰናል (4-2-3-1): ኦስፒና፣ ቤለሪን፣ ሙስታፊ፣ ኮሺየልኒ፣ ሞንሪል፣ ዠካ፣ ራምሴ፣ ኦዚል፣ ዊልሼር፣ ሚክሂታሪያን፣ ላካዜቴ

Advertisements