ሹመት / ስቴቨን ጄራርድ የሬንጀርስ አሰልጣኝ ሆኖ በይፋ ተሾመ

​ለ 19 አመታት ለሊቨርፑል በመጫወት 2016 ላይ በጡረታ የተገለለው ስቴቨን ጄራርድ የስኮትላንዱ ሬንጀርስ አሰልጣኝ ሆኖ በይፋ ተሾመ።

37ኛ አመቱ ላይ የሚገኘው ጄራርድ ጥቅምት ወር ላይ ፔድሮ ካይቲንሀ ከተሰናበቱ በኋላ በጊዚያዊ አሰልጣኝነት ሬንጀርስን እየመሩ የነበሩት ገራም ሙርቲን ተክቶ ወደ አይብሮክስ አቅንቷል።

ለአራት አመታት ሬንጀርስን ለማሰልጠን የተስማማው ጄራርድ ከአዲሱ አመት የዝግጅት ጊዜ ጀምሮ ስራውን የሚጀምር ይሆናል።

ዛሬ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ “ቀጣዩ የሬንጀርስ አሰልጣኝ ሆኜ በመሾሜ ኩራት ተሰምቶኛል።በዚህ ክለብ ታሪክ እና ባህል ብዙ ክብር አለኝ፣ስራዬንም እስክጀምር ጓጉቻለው።”በማለት ጄራርድ ስለ አዲሱ ስራው ተናግሯል።

ጄራርድ አብረውት ቡድኑን በማሰልጠን የሚያግዙት የአሰልጣኞች ስታፍ በቀጣይነት እንደሚታወቁ ክለቡ ጨምሮ አሳውቋል።

የቀድሞው ተጫዋች በ 19 አመት የሊቨርፑል ቆይታው 710 ጨዋታዎችን ተጫውቶ የፕሪምየርሊጉን የዋንጫ ክብር ሳያሳካ ጡረታ ቢወጣም ከቀዬቹ ጋር ዘጠኝ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችሏል።

ለሀገሩም 114 ጊዜ መጫወት የቻለ ሲሆን ከስድስት ታላላቅ ውድድሮች ውስጥ ሶስቱን በአንበልነት መርቷል።

ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ 2016 ላይ ጫማውን የሰቀለው ጄራርድ ወደ ሊቨርፑል ተመልሶ የወጣት ቡድኑን ሲያሰለጥን ከቆየ በኋላ ወደ ሬንጀርስ ማቅናቱ ዛሬ በይፋ እርግጥ ሆኗል።

ጄራርድ በአይብሮክስ

የሬንጀርስ ሊቀመንበር ዴቭ ኪንግ እንዳሉት “ከመጀመሪያው ጀምሮ ውይይታችን በመልካም ሁኔታ ተጉዟል።ጄራርድ ሬንጀርስን ወደ ተሻለ ቦታ እንደሚያደርሰው እምነቱ አለን

“በውይይታችን ጊዜ አስደናቂ ነበር።እኛም እሱ የሚያስፈልገውን እውቀት እንዳለው እና ክለቡንም ውጤታማ እንደሚያደርገው እምነቱ አለን።ይህ ለሱ፣ለክለባችን እና ለደጋፊው የተለየ እለት ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።

ጄራርድ ዛሬ በአይብሮክስ ስታድየም ተገኝቶም ከደጋፊዎች ጋር የተገናኘ ሲሆን ደማቅ አቀባበልም ተደርጎለታል።

Advertisements