ፖል ካጋሜ ለአርሴናል ውድቀት የክለቡ ባለቤቶች ተጠያቂ መሆናቸው አሳወቁ

የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት እና የአርሴናል ደጋፊ የሆኑት ፖል ካጋሜ መድፈኞቹ ከዩሮፓ ሊጉ ውጪ ከሆኑ በኋላ ለክለቡ ውጤት ማጣት ተጠያቂዎቹ ባለቤቶቹ መሆኑን አሳወቁ።

መድፈኞቹ የ 2017/2018 የውድድር ጊዜን በአትሌቲኮ ማድሪድ ከተሸነፉ በኋላ ያለ ዋንጫ ማጠናቀቃቸውን እርግጥ ሆኗል።

ቡድኑ ወደ ቻምፕየንስ ሊግ ሊመለስበት የሚችልበት ብቸኛ አማራጩ ከነበረው የዩሮፓ ሊግ ውድድር ከግማሽ ፍፃሜው ሳይሻገር ቀርቷል።

ትናንት ምሽት በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ በአትሌቲኮ ማድሪድ በመሸነፋቸው ለክለቡ የረጅም ጊዜ አሰልጣኝ የሆኑት አርሴን ዌንገር ጭምር መጥፎ ምሽት ሆኖ አልፏል።

በተለይ ዌንገር ከክለቡ ጋር በአመቱ መጨረሻ ጀምሮ እንደሚለቁ ካሳወቁ በኋላ በአውሮፖ መድረክ የመጨረሻ ተሳትፏቸውን በዋንጫ አጅበው ስንብታቸውን ያሳምራሉ ተብሎ ቢጠበቅም አልተሳካላቸውም።

ቡድኑ በሊጉ ላይ እስከ አራተኛ ሊያጠናቅቅ የሚችልበት እድልም ባለመኖሩ መድፈኞቹ በድጋሚ በቀጣይ አመት በዩሮፓ ሊግ ተሳትፏቸው የሚቀጥሉ ይሆናል።

ይኸው የክለቡ ውጤት አልባ ጉዞ የክለቡ ደጋፊዎችን ጭምር ያሳዘነ በመሆኑ ትችታቸውን እያቀረቡ የሚገኙ በርክተዋል።

ከዚሁ ከጎረቤት የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት የሆኑት ፖል ካጋሜ ሀሳባቸውን ከሰጡ ውስጥ ይገኙበታል።

ፕሬዝዳቱ በትዊተር ገፃቸው ላይ “አርሰናል በጨዋታ ጥሩ ቡድን ነው።አሰልጣኙም አርሴን ዌንገር በጣም ጥሩ ናቸው።ይህ ሽንፈት የዘመን መጨረሻ አይደለም።

“አሰልጣኙ ክለቡን ያለ ዋንጫ ይለቃሉ።እኔ አሁንም የክለቡ ደጋፊ ሆኜ እቀጥላለው።ለክለቡ ውጤት ማጣት መወቀስ ያለባቸው ግን የክለቡ ባለቤቶች ናቸው።” ሲሉ ተናግረዋል።

ካጋሜ ቡድኑ ለውጥ እንደሚያስፈልገው እና ወደነበረበት እንደሚመለስ እምነቱ እንዳላቸው ጨምረው ገልፀዋል።

Advertisements