የሊቨርፑል የበላይ አራት ውስጥ ገብቶ መጨረስ “ትልቅ ስኬት” እንደሆነ ክሎፕ ገለፁ

የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ በዚህ የፕሪሚየር ሊጉ የውድድር ዘመን ቡድናቸው ከእንደ እስከአራት ባለው ደረጃ ውስጥ ገብቶ ማጠናቀቅ ከቻለ “ታላቅ ስኬት” እንደሚሆናቸው ያምናሉ።

የክሎፕ ቡድን ባልተተበቀ ሁኔታ አስገራሚ የሻምፒዮስ ሊግ ጉዞ በማድረግ ለፍፃሜ ደርሷል። ነገር ግን በቀጣዩ የውድድር ዘመን በዚህ ውድድር ላይ ዳግመኛ ተሳታፊ መሆናቸውን እስካሁን ማረጋገጥ አልቻሉም።

በጀርመናዊው አሰልጣኝ የሚመራው ሊቨርፑል በሶስተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ በስድስት ነጥቦች የሚበልጠውን ቼልሲን እሁድ ምሽት ይገጥማል። ይሁን እንጂ ተጋጣሚያቸው ከርእነሱ የሚበልጥ ቀሪ ጨዋታዎች አሉት።

ይህን ተከትሎም ክሎፕ ቡድናቸው የበላይ አራት ደረጃ ውስጥ ገብቶ ማጥናቀቅ ከቻለ የውድድር ዘመኑ ስኬታማ እንደሚሆንለቸው ተናግረዋል።

“ትልቅ ነገር ይሆናል። የውድድር ዘመኑን ስንጀምር በእርግጥም ዋነኛው ዒላማችን ይኸው ነበር።” ሲሉ ለእንግሊዝ ጋዜጦች ተናግረዋል።

“ሻምፒዮን መሆን ትፈልጋለህ። ነገር ግን ከተወሰኑ ጥቂት ወራት በኋላ ያ የሚሆን እንዳልሆነ ግልፅ ይሆንልሃል።

“ዒላማችን ለሻምፒዮንስ ሊጉ መብቃት ነው። ያ ደግሞ ትልቅ ስኬት ይሆናል። ባለን የቡድን ስብስብ፣ ለፍፃሜ የበቃንበት መንገድ እና በሁሉም ዘርፍ በትልቅ ተነሳሽነት እንደመጫወታችን እና ዳግመኛ ዝግጁ እንደመሆናችን እንዲሁም ካሉብን ጉዳቶች አንፃር ይህ ታላቅ ስኬት ነው። እኛም በትክክል የምንፈልገው ይህንኑ ነው።

“ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ እበቃለሁ ብለህ ልታቅድ እንደማትችል ግልፅ ነው። የውድድር ዘመኑ ሲጀመር ማንም ሰው ስለዚያ አላሰበም።

“በእርግጥ የተቻለንን ያህል ርቀት ለመጓዝ ፍላጎት ነበረን። ነገር ግን የእኔ አብይ ዒላማ የነበርው የበላይ አራት ደረጃ ውስጥ መግባት ነበር። ለእዚህም ጠንክረን ሰርተናል። በመሆኑም ዕቅዳችንን ማሳካት እንሻለን።”

ሊቨርፑል በውድድር ዘመኑ መገባደጃ ወቅት እንደኤምሬ ቻን፣ አሌክስ ኦክስሌድ-ቻምበርሌን እና ዦል ማቲፕን በጉዳት አጥቷል። ነገር ግን በጉዳት ላይ የነበረው አደም ላላና ወደጨዋታ ለመመለስ ተቃርቧል።

ክሎፕም በውድድር ዘመኑ እስካሁን ላደረጉት ጥረት ተጫዋቾቻቸውን አወድሰዋል።

“የውድድር ዘመኑ ለበርካታ ተጫዋቾች አስቸጋሪ ነበር።” በማለት ተናግረው “በየግል እዚም እዚያም በእኛ ላይ ችግሮች ነበሩ። ነገር ግን በግንኙነታችን ላይ በሚገባ ጠንካራ ሆነን መስመራችንን ሳንስት ዘልቀናል። ይህ ባይሆን ኖሮ በሊጉ ሶስተኛ እና ለሻምፒዮንስ ሊጉ ፍፃሜ ለደርስንበት ለዚህ ደረጃ አንበቃም ነበር። ጨርሶ ይህ ሊሆንም አይችልም ነበር።

“ሁሉም ነገር የተጫዋቾቹ ጥረት ነው። እስካሁን ያደረጉልን ነገር ፍፁም ልዩ ነው። ችግሩ የእሁዱም ጨዋታ ቢሆን ፋይዳ ያለው መሆኑ ነው።”

Advertisements