ድንገተኛ / የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ድንገተኛ ቀዶ ጥገና 

የማንችስተር ዩናይትድ ምልክት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ለቀዶ ጥገና ያበቃቸው ድንገተኛ ህመም መላው የአለም የእግርኳስ ወዳጅን ያስደነገጠ ሆኗል።ጤንነታቸውም እንዲመለስ መልካም ምኞት ከየአቅጣጫው እየደረሳቸው ይገኛል።

ቅዳሜ ምሽት በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጤንነት ዙሪያ የተሰማው ወሬ ታላላቅ ሚዲያዎች ጭምር ልዩ ትኩረት ሰጥተውት የዘገቡት ነበር።

አንጋፋው የቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ በጭንቅላታቸው ውስጥ ደም በመፍሰስ ያጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም በሆስፒታል በልዩ ክትትል ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል።

ምሽቱ ላይም በወጡ መረጃዎች መሰረት ፈርጊ የተሳካ ቀዶጥገና የተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል።

2013 ላይ ጡረታ እስኪወጡ ድረስ ለ 27 አመታት በዩናይትድ የቆዩት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስለ ህመማቸው ክለቡ በመግለጫው “ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ድንገታዊ ቀዶ ጥገና ዛሬ አድርገዋል።ሂደቱም በመልካም መንገድ ተከናውኗል።ነገርግን በደንብ እስኪያገግሙ  ድረስ ለተወሰኑ ቀናት ክትትል ይደረግላቸዋል።” በማለት አሳውቋል።

የ 76 አመቱ ፈርጊ በመጀመሪያ በቺሻየር ከሚገኘው ቤታቸው በአንቡላንስ ማክልስፊልድ ወደሚገኘው ሆስፒታል ተወስደዋል።

በመቀጠልም ምሽቱ ላይ ቀዶጥገና ወደተደረገላቸው ሳልፎርድ ሮያል ሆስፒታል በፖሊስ ታጅበው እንዲያቀኑ ተደርገዋል።

የፈርጊ ህመም ይፋ ከመሆኑ በፊት ጥርጣሬዎቹ ወደ እውነት የወሰደው መረጃ የተገኘው የፈርጊ ልጅ በሆነው ዳረን ፈርጉሰን የሚሰለጥነው ዶንካስተር ሮቨርስን በሊግ አንድ የመጨረሻ ጨዋታው ላይ ያለ ዋና የቡድኑ አሰልጣኝ ከተጫወተ በኋላ ነው።

ዳረን ፈርጉሰን ዶንክስተርን ለመምራት ያልቻሉበት ምክንያት በቤተሰብ ችግር እንደሆነ ተጠቅሷል።

ፈርጊ ህመማቸው ከተሰማ በኋላ የቀድሞ ተጫዋቾቻው ጨምሮ የተቃራኒ ቡድን እና መላው የእግርኳስ ወዳጆች ወደ ጤንነታቸው እንዲመለሱ መልካም ምኞታቸውን እያደረሱ የሚገኙ ሲሆን እሳቸውም በልዩ ክትትል በሆስፒታሉ ውስጥ ይቆያሉ።

Advertisements