ትየሪ ሄነሪ በአርሴን ዌንገር የስንብት ጨዋታ በኢምሬትስ አለመገኘቱ እየተተቸ ይገኛል

ፈረንሳዊው የቀድሞ የመድፈኞቹ ኮከብ እና በአርሴን ዌንገር ቆይታ ወደ ታላቅ ተጫዋችነት የተቀየረው ትየሪ ሄነሪ በአርሴን ዌንገር የስንብት ጨዋታ ላይ በኤምሬትስ ከመገኘት ይልቅ ማን ሲቲን ዋንጫ ሲያነሳ ለመመልከት በኢትሀድ  መገኘቱ እየተተቸ ይገኛል።

ዌንገር “ሜርሲ አርሴን” በሚሉ የምስጋና መልእክቶች በደማቅ ሁኔታ በተሸኙበት እለት አርሴናል በርንሌን 5-0 ማሸነፍ ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቀድሞ ተጫዋቾቻቸው በተገኙበት በይፋ የተሸኙት ዌንገር 22 አመት የቆዩበትን ክለብ እና ደጋፊዎች ደህና ሁኑ ሲሉ ተሰናብተዋል።

በእሁዱ የመጨረሻ የሜዳቸው ጨዋታ ላይ ትኩረት በሳበ መልኩ ሲሰናበቱ ከክለቡ ጋር ቁርኝነት ያላቸው የቀድሞ ተጫዋቾች እና ከ 100 በላይ ለክለቡ የተሰለፉ ተጫዋቾች ሲገኙ የትየሪ ሄነሪ በቦታው አለመገኘት አስገራሚ ሆኗል።

ሄነሪ አርሴን ዌንገር ካስፈረሙት በኋላ በአርሰናል ስመገናና መሆን የቻለ ሲሆን በእግርኳስ ህይወቱ ላሳየው እድገት የአርሴን ዌንገር አስተዋፅኦ ቀላል ባለመሆኑ በሽኝቱ እለት እንደሚገኝ ተጠብቆ ነበር።

ነገርግን ሄነሪ በኤምሬትስ ከመገኘት ይልቅ በተንታኝነት ከሚሰራበት ስካይ ስፖርት ጋር ማንችስተር ሲቲ ዋንጫ ሲያነሳ ለመመልከት በኢትሀድ መገኘቱ ለትችት ዳርጎታል።

የቀድሞ የስካይ ስፖርቱ አንዲ ግሬይ ሄነሪን ከተቹት ውስጥ ይገኝበታል።

“በኤምሬትስ ባለመገኘቱ በጣም ተገርሚያለው።ከ 100 በላይ ለክለቡ የተጫወቱ ከአልጣኙ ክብር እና ሽኝት ተገኝተው ነበር።

ሄነሪ ግን ምንም ትርጉም ለሌለው የሲቲ ጨዋታ ለመመልከት በኢትሀድ ነበር።ይህ ደግሞ ብዙ ነገር የሰሩለት ዌንገርን አለማክበር ነው።” ሲል ተችቶታል።