ወቅታዊ / የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ወቅታዊ የጤና ሁኔታ

ባለፈው ቅዳሜ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በጭንቅላት ደም መፍሰስ ምክንያት ቀዶ ጥገና ማድረጋቸው ከተሰማ በኋላ አሁን ደግሞ የቅርብ ጓደኞቻቸው ስለ ወቅታዊ የጤንነት ሁኔታቸው መረጃ ሰጥተዋል።

መላው አለምን ያስደነገጠው ዜና የወጣው ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የነበረ ሲሆን ማንችስተር ዩናይትድም በይፋዊ ገፁ ላይ የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ህክምና በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን ማረጋገጫ መስጠቱ ይታወሳል።

13 የፕሪምየርሊግን ዋንጫ በማንሳት በዩናይትድ ቤት ውስጥ ስማቸውን የተከሉት ፈርጊ ወደ ሮያል ሆስፒታል በፖሊስ ታጅበው ካቀኑ በኋላ ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸዋል።

እድሜያቸው በመግፋቱ እና ህመሙ ልዩ ክትትል እንደሚያስፈልገው ተገልፅ በሚስጢር ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ሳይሰማ ሁለት ቀኖች አልፈዋል።

ነገርግን ያጋጠማቸው የጤና እክል ላለፉት ቀናት’ ኮማ ‘ውስጥ ገብተው እንደነበር እየወጡ የነበሩ መረጃዎች ሲያመለክቱ ቆይተዋል።

አሁን ግን የእንግሊዙ ዴይሊ ሜይል ከፈርጊ የቅርብ ጓደኞች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ሰር አሌክስ ገብተውት ከነበረው አስቸጋሪ የጤና እክል ሁኔታ መንቃታቸውን አሳውቋል።

ጓደኞቻቸው ጨምረው ፈርጊ በሆስፒታል ውስጥ ቁጭ ብለው ስለ ጤንነታቸው ሁኔታ መጠየቅ መጀመራቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

መረጃው ከቤተሰቦቻቸው እና ከማን ዩናይትድ ክለብ ማረጋገጫ ባያገኝም የጤንነታቸው ሁኔታ ግን መጀመሪያ ከነበረው መሻሻል ማሳየቱን ነው የታወቀው።

የፈርጊ ህመም ከተሰማ በኋላ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የድጋፍ መልእክቶችን አሁንም መድረሳቸው ቀጥለዋል።

Advertisements