ቬንገር በፒኤስጂ የቀረበለቸውን የዋና ስራአስኪያጅነት ሚና ጨርሶ ውድቅ አላደረጉትም

አርሰን ቬንገር በውድድር ዘመኑ መጨረሻ አርሰናልን ሲለቁ ከፒኤስጂ የቀረባቸውን የዋና ስራ አስኪያጅነት ሚና የመረከቡን ሃሳብ ጨርሶ ውድቅ አላደረጉትም።

የ68 ዓመቱ አሰልጣኝ 22 ዓመታት ለሚጠጉ ጊዜያት ከቆዩበት የመድፈኞቹ አሰልጠኝነት ሚና እንደሚለቁ ይፋ ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ “ከጠበቁት በላይ የሆነ” የስራ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።

ቬንገር የፒኤስጂው ዋና አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ ምትክ እንዲሆኑ ወይም የከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ሚና እንዲኖራቸው ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ምንም እንኳ ፈረንሳያዊው ሰው በአሰልጣኝነት ሚና እንደሚቀጥሉ ቢሰማቸውም፣ የሃሳብ ለውጥ ሊያደረጉም እንደሚችሉም ገልፀዋል።

“የዋና ስራአስኪያጅነት ሚና? ያ ውሳኔ ላሳልፍበት የሚገባ ጉዳይ ነው።” ሲሉ ቬንገር አርሰናል ረቡዕ ምሽት ወደሌስተር ተጉዞ ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት ባደረጉት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልፀዋል።

“አሁን ውሳኔ ላክ አልደረስኩም። [የአሰልጣኝነት ሚናውን] እሺ እላለሁ። ወዲያውኑ [መልሴ] አዎ ነው። ነገር ግን ብዙ ቆይቼ ‘አይሆንም አሁን በተወሠነ መልኩ የአቅጣጫ ለውጥ የማደርግበት ጊዜ ነው።’ ብዬ አስብም ይሆናል። ከምር ግን ምንም አይነት ምልስ ልሰጣችሁ አልችልም። አላውቅም።”

ቬንገር ወደፓርክ ደስ ፕሪንስስ እንዲያመሩ ከፒኤጂው ፕሬዝዳንት ናስር አል-ከኸላይፊ ዘንድ ማበረታቻ እንደቀረበላቸው የጭምጭምታ ዘገባዎች አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ አሰልጣኙ የአል-ከኸላይፊ ብሮድካሲንግ ኔትዎርክ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለሆነው ቢኢን ስፖርትስ ጋር ባላቸው የተንታኝነት ሚና ጋር በተያያዘ ብቻ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረው ግለሰቡ በዕቅዳቸው ላይ ተፅእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚባለውንም አስተባብለዋል።

“ከናስር ጋር ያለኝ ግንኙነት ይበልጥ ሚዲያ ላይ የተመሰረተ ነው።” ሲሉ ቬንገር ተናግረው “እሱ ገና በአፍላ ዕድሜው ስራውን ጀምሯል። እኔም የመጀመሪያው ኮንትራቱ – የመጀመሪያ ፈራሚው ነኝ። እናም ለዚህ ነው ጥሩ ግንኙነት ያለን። በመሆኑም ሁልጊዜም ከቢኢን ጋር ነበርኩ። ነገር ግን ያ በየትኛውም ውሳኔዬ ላይ ተፅእኖ አያስድርም።”

ቬንገር አክለውም ከአርሰናል የለንደኑ ኮልኔይ የልምምድ ሜዳ ርቀው የሚያሳልፏቸው ቀናት በእጅጉ ከባድ እንደሚሆኑባቸውም ገልፀዋል።

“በእርጥም በየቀኑ ወደዚያ በማምራቴ ደስተኛ ነበርኩ። ታውቃላችሁ በ22 ዓመታት ጊዜ ውስጥ አንድም የልምምድ ጊዜ አልፎኝ አያውቅም። ፈፅሞ በቢሮዬ ውስጥ ቆይቼ አላውቅም። በየቀኑ በዚያ እገኛለሁ።” ሲሉ ቬንገር ተናግረዋል።

“ይህም የምናፍቀው ነገር ነው። አረንጓዴ ሳር እወዳለሁ። ሁልጊዜም ጠዋት በዚያ ላይ መረማመድም የምወደው ነገር ነው።” በማለትም ጨምረው ተናግረዋል።