የማንችስተር ሲቲ የ2018/19 የውድድር ዘመን አዲስ መለያ ይፋ ሆነ

ማንችስተር ሲቲ የ2018/19 የውድድር ዘመን አዲስ መለያውን ይፋ አድርጓል።

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ሲቲ ያለፈው እሁድ በመውረድ አደጋ ውስጥ ይገኝ ከነበረው ኸደርስፊልድ ጋር ያለግብ በአቻ ውጤት ከተለያየ በኋላ በይፋ የሊጉን ዋንጫ አንስቷል።

ክለቡ ዛሬ ምሽት ብራይተንን በሚገጥምበትና በውድድር ዘመኑ በሜዳው በሚያደረገው የመጨረሻ ጨዋታ አዲሱን ትጥቅ ለማጀመሪያ ጊዜ ለብሶ የሚጫወትም ይሆናል።

እንደአሜሪካኑ የትጥቅ አምራች ናይክ ድረገፅ መረጃ ከሆነ አዲሱ የሲቲ መለያ “የክለቡን ቁልፍ የታሪክ አጋጣሚዎች መሰረት በማድረግ የ2018/19 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ መለያ የሲቲን ተለምዷዊ ሰማያዊው ቀለም፣ በእጅጌውና ትከሻዎቹ ደብዘዝ ያለ ጥቁር ሰማያዊ መስመሮች ዘፍረውበት የተዘጋጀ ነው።

“የቪ ቅርፅ ባለው አንገትጌው ላይ ባለው ጥቁር ሰማያዊ መስመር ላይ “ሰማያዊ ጨረቃ” የሚል በክለቡ ደጋፊዎች የሚዜመው ዝነኛ ሃገረግም ሰፍሮበታል።”

የክለቡ የመለያ አልባሳት አካል የሆነው ቁምጣም ክለቡ በ1937 የሊጉ ሻምፒዮን በነበረበት ዘመን የለበሰው አይነት ቀለም ያለው ሆኖ ተዘጋጅቷል።

የፔፕ ጋርዲዮላው ማንችስተር ሲቲ ዛሬ ምሽት ብራይተንን የሚረታ ከሆነ በአንድ የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ብዙ ጨዋታዎችን በማሸነፍ 30 ጨዋታዎችን መርታት ከቻለው ቼልሲ በመብለጥ አዲስ ክብረወሰን የሚጨብጥ ይሆናል።

በሲቲ የወንዶችና ሴቶች ቡድን የሚለበሰው አዲሱ መለያ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 6፣ 2010 ዓ.ም በይፋ ለገበያ የሚቀርብ ይሆናል።

Advertisements