የኡመድ ኡኩሪው ሰሞሀ ለግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ ደረሰ

ኢትዮጵያዊው ኡመድ ኡኩሪ በአጥቂነት የሚመራው የግብፁ ሰሞሀ በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ የግብፅ ዋንጫ ፍፃሜ መድረሱን አረጋግጧል።

የአልሀሊ የበላይነት በሚገባ የሚታይበት የግብፅ ፕሪምየርሊግ ላይ የሌሎች ቡድኖች አሸናፊነት በጥሎማለፍ የዋንጫ ጨዋታዎች ካልሆነ በቀር በፕሪምየርሊጉ ላይ የአልሀሊን ሀያልነት መስበር አልቻሉም።

የሚገርው ሌላው የሀገሪቷ ታላቅ ቡድን የሆነው ዛማሌክ እንኳን ታላቅነቱን በውስጥ የፕሪምየርሊግ ጫወታዎች ማሳየት ተስኖት የአል አህሊ አጃቢ ከሆነ አመታት እየተቆጠሩ ይገኛሉ።

አሁን ላይ መናገር የሚቻለው አል አህሊ እንደ ጀርመኑ ባየርን እና እንደ ጣሊያኑ ጁቬንቱስ ሁሉ ከአመት አመት በውስጥ የፕሪምየርሊግ ውድድር ላይ በፍፁም የበላይነት አሸናፊነቱን እያወጀ መቀጠሉን ሲሆን ቀሪዎቹ የግብፅ ቡድኖች በተመጣጣኝ ፉክክር የሊጉን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት እንዲሁም በጥሎማለፍ የግብፅ ዋንጫ ላይ ትኩረት ማድረግ ሆኗል።

ዘንድሮም እንዲሁ የሊጉ ዋንጫ ቀደም ብሎ በአልሀሊ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ላለፉት አመታት እንደሆነው ሁሉ ቡድኖች የጥሎማለፉን ዋንጫ ላይ ሲፋለሙ ቆይተዋል።

ጠንካራ ጨዋታዎችን አልፈው ለፍፃሜ መቅረብ የቻሉት ደግሞ ዛማሌክ እና ሰሞሀ ሆነዋል።

በተለይ ሰሞሀ በኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ የሚመራ ሲሆን ምሽት ላይ ለፍፃሜ ባደረገው ጨዋታ ላይ አል አሲኦቲን በመለያ ምት ማሸነፍ ችሏል።

አል አሲኦቲን ወደ ግማሽ ፍፃሜ የደረሰው ታላቁን አልሀሊን አሸንፎ በመሆኑ ለሰሞሀ በቀላሉ እጅ እንደማይሰጥ ሲጠበቅ ቆይቷል።


በምሽቱ ጨዋታ 72ኛው ደቂቃ ላይ ሰሞሀ በግብፃዊው አህመድ ተምሳህ ጎል መሪ ሆነው አሸናፊ ለመሆን እስከ መጨረሻው ደቂቃ ቢጠብቁም ግብጠባቂው ኤል ማህዲ ሶሊማን በናሚባዊው ቤንሰን ሺሎንጎ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ምክንያት ጨዋታው 1-1 ተጠናቆ ወደ ተጨማሪ ሰአት አምርቷል።

በጭማሪው ሰአትም በሁለቱም በኩል ጎል ባለመገኘቱ ወደ መለያ ምት ካቀኑ በኋላ ሰሞሀ 4-2 አሸንፏል።ለአል አሲኦቲ ሺሎንጎ እና አህመድ ሰኢድ ኦካ የመለያ ምቱን ስተዋል።

ውጤቱ ሰሞሀ በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ ለግብፅ ዋንጫ እንዲቀርብ ያስቻለው ሲሆን ዋንጫውን ለማንሳት ከፊቱ ያለውን ዛማሌክ በቀጣይ ማክሰኞ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ሰሞሀ 2014 ላይ በተመሳሳይ ለፍፃሜ ቀርቦ በአሁኑ ተፋላሚው ዛማሌክ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ተሸንፎ ዋንጫውን ማግኘት ሳይችል ቢቀርም በድጋሚ ዘንድሮ ሁለቱ ቡድኖች በመገናኘታቸው የ 2014 ቱን የፍፃሜ ጨዋታ መበቀል የሚችልበት አጋጣሚ አግኝቷል።

ዋንጫውን ማንሳት የሚችል ከሆነ ደግሞ ከቡድኑ ባለፈ ለ ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ ትልቅ ስኬት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ምስል – ከሶከር ኢ እና ሰሞሀ ገፅ የተወሰደ

Advertisements