ባርሴሎና በቀጣይ ሳምንት ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር እንደሚጫወት አሳወቀ

የስፔኑ ሻምፕዮን ባርሴሎና ከአብሳ ፕሪምየርሺፑ ሻምፕዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በቀጣይ ሳምንት እንደሚጫወት አሳውቋል።

ለ 21 ጊዜያት ያህል ወደ አፍሪካ በመምጣት መጫወት የቻለው ባርሴሎና በቀጣይ ሳምንት ወደ ጆሀንስበርግ በማቅናት ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ለሁለተኛ ጊዜ ይገጥማል።

ሳይሸነፍ የላሊጋ ዋንጫን ለማንሳት ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ የቀረው ባርሴሎና የኔልሰን ማንዴላ 100ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በሚኖረው ክብረበአል ላይ ሰንዳውንስን እንደሚገጥም አረጋግጧል።

ሁለቱ ቡድኖች እንደሚጫወቱ የተሰማው ባለፈው ሳምንት ቢሆንም የካታላኑ ቡድን መረጃውን ማረጋገጥ የቻለው ግን ዛሬ ነው።ከጨዋታው አንድ ቀን ቀን ቀደም ብለውም ወደ ጆሀንስበርግ እንደሚያቀኑ ጨምረው አሳውቀዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በፈረንጆቹ ግንቦት 16 የሚካሄድ ሲሆን በደ/አፍሪካ የሚገኙ የባርሴሎና ደጋፊዎች ቡድኑን በቅርበት የመመልከት እድል እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።

የላሊጋው ሻምፕዮን ከዚህ ቀደም 2007 ላይ ወደ ደ/አፍሪካ መጥቶ ፕሪቶሪያ ላይ ሰንዳውንስን ጋጥሞ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ጨዋታውን 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል።

በአጠቃላይ በአፍሪካ ምድር ያደረገው ጨዋታም 18ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይቶ አንድ ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።

Advertisements