አርዳ ቱራን ዳኛን በመግፋቱ ሪከርድ የሆነ ቅጣት ተቀጣ

የቱርክ ፕሮፌሽናል እግርኳስ የስነምግባር ቦርድ የባሳክሽር አማካይ የሆነው አርዳ ቱራን ላይ ዳኛን በመግፋቱ ምክንያት ሪከርድ የሆነ ቅጣት ማስተላለፉን አሳወቀ።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በቱርክ ሱፐርሊግ በተካሄደው ጨዋታ ላይ ከባርሴሎና ወደ ቱርክ አቅንቶ በውሰት ለባሳክሺር እየተጫወተ የሚገኘው አርዳ ቱራን የእለቱ ረዳት ዳኛን ገፍቷል።

በጨዋታው ሲቫስቶር እና ባሳክሺር 1-1 የተለያዩ ሲሆን ቱራን ዳኛው ላይ ያልተገባ ስድብ በመሳደብም ዳኛውን ሲያስፈራራ ታይቷል።

ተጫዋቹ “አታፍሩም እንዴ? ሁላችሁም መሞት ትፈልጋላችሁ?”በማለት ዳኛው ላይ ሲዝት እንደነበር ታውቋል።

በጨዋታው በቀይ ከሜዳ እንዲወጣ ቢደረግም ንዴቱ ተፋፍሞ ያልተገባ ባህሪ አሳይቷል።

ቡድኑም ለዋንጫ የሚያደርገውን ጉዞ በአቻ ውጤት በማጠናቀቁ ሁለት ጨዋታዎች በቀሩት ሊግ ላይ በጋላታሳራይ በሶስት ነጥቦች ተቀድሞ ተስፋው ተሟጧል።

በእለቱ ንዴቱን መቆጣጠር ያልቻለው ቱራን በመግፋቱ 10 ጨዋታዎችን፣በመሳደቡ ሶስት ጨዋታዎችን እንዲሁም ዳኛን በማስፈራራት ተጨማሪ ሶስት ጨዋታዎች በአጠቃላይ 16 ጨዋታዎች እንዳይጫወት ተቀጥቷል።

ቱራን በተጨማሪም 9200 ዲላር የተቀጣ ሲሆን ቅጣቱም እስከ ቀጣዩ የውድድር አመት አጋማሽ ድረስ ወደ ሜዳ እንዳይመለስ የሚያደርገው ይሆናል።

የቡድን አጋሩ ጆሴ ማርሲዮ ዳ ኮስታ እንዲሁ ባልተገባ ባህሪ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ተጥሎበታል።

ቱራን በባርሴሎና በቋሚነት ለመጫወት ባለመቻሉ ለባሳክሺርን ለ ሁለት አመት ከግማሽ በውሰት የተቀላቀለ መሆኑ ይታወሳል።

Advertisements