ሞሪንሆ፡ የደ ኽያ የወርቅ ጓንት ሽልማት የማንችስተር ዩናይትድ ነፀብራቅ ነው

የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ የፕሪሚየር ሊጉን የወርቅ ጓንት ያሸነፈውን ዴቪድ ደ ኽያን አድንቀው ሽልማቱ ለቡድኑም ጭምር እንደሆነ ገልፀዋል።

ደ ኽያ ማንችስተር ዩናይትድ ሃሙስ ምሽት ከዌስትሃም ጋር ያለግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ በዚህ የውድድር ዘመን ለ18ኛ ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር መውጣቱን ተከትሎ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ተብሎ የወርቅ ጓንት ሽልማቱን ማግኘት ችሏል።

“ዴቪድ ድንቅ ነበር።” ሲሉ ሞሪንሆ ለማንችስተር ዩናይትድ ቴሌቪዥን ተናግረው “ነገር ግን የወርቅ ጓንቱ የቡድኑም ጭምር ነው። እናም ማንም ሰው ግብ ጠባቂውን ብቻ ግምት ውስጥ በሚያስገባበትና እሱ የፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂ ብቻ ነው ብሎ የሚናገርበትም አይደለም።

“ጉዳዩ መረብን ያለማስስደፈር ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ የቡድኑም ጭምር ነው። ሁላችንም በዴቪድ ደስተኛ መሆናችን ግልፅ ነው። ይህ ደግሞ የአንድ ታላቅ የቡድን ስኬት ነው።” ብለዋል።

ደ ኽያ በዌስት ሃሙ ጨዋታ መረቡን አለማስደፈሩ ከተፎካከሪው የማንችስተር ከተማ ተቀናቃኙ የሲቲ ግብ ጠባቂ ኤደርሰን ልቆ የወርቅ ጓንቱን ማሸነፍ ችሏል።

ባለፈው የውድድር ዘመን የዚህ ሽልማት አሸናፊ የነበረው ቲቡዋ ኮርትዋ የነበረ ሲሆን፣ ከደ ኽያ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ የወርቅ ጓንቱን ማሸነፍ የቻለው የማንችስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ ደግሞ በ2008-09 የውድድር ዘመን ሽልማቱን ማግኘት ችሎ የነበረው ኤድዊን ቫንደርሳር ነበር።

ስሙ ከአውሮፓው ሻምፒዮን ሪያል ማድሪድ ዝውውር ጋር ተያይዞ የሚገኘው ደ ኽያ ያገኘውን ሽልማት አስመልክቶ “ደስ የሚል ስሜት አለው። ይህ የመጀመሪያዬ የወርቅ ጓንት ነው።

“በዚህም ደስተኛ ነኝ። ይህ ማለት በሊጉ ላይ ጥሩ እንከላከል ነበር ማለት ነው። በራሴም ሆነ በቡድኑ ደስተኛ ነኝ።

“ሽልማቱ ለሁላችንም ነው። የቡድኑ ሽልማት ነው። ለግብ ጠባቂ ብቻም አይደለም። ለእኔ ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን እኔም በቡድኑ ደስተኛ ነኝ።” ሲል የ27 ዓመቱ ስፔናዊ ግብ ጠባቂ ተናግሯል።

Advertisements