ሊዮ ሜሲ ለ አምስተኛ ጊዜ የአውሮፓ የወርቅ ጫማ አሸናፊ ሆነ

የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ሊዮ ሜሲ ለአምስተኛ ጊዜ የአውሮፓ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን የወርቅ ጫማ አሸናፊነቱን አረጋግጧል።

ሁለት ጨዋታዎች በቀሩት የላሊጋ የዘንድሮ ውድድር 34 ጎሎችን ለባርሴሎና ማስቆጠር የቻለው ሊዮ ሜሲ ለአምስተኛ ጊዜ የአውሮፓ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።

ሜሲን በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው ሲከተሉት የነበሩት ሞ ሳላህ እና ሮበርት ሌዋንዶውስኪ የነበሩ ቢሆንም ሁለቱም የሊጋቸውን ጨዋታዎች በማጠናቀቃቸው ሜሲ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት የአውሮፓ የወርቅ ጫማ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል።

ተጫዋቹ በምሽቱ ጨዋታ ሌቫንቴን ከሚገጥመው የቡድን ዝርዝር ውጪ የሆነ ቢሆንም በላሊጋው የመዝጊያ ጨዋታ ላይ ከሪያል ሶሴዳድ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ወደ ሜዳ ይመለሳል።

ይህ ደግሞ አሁን ያስቆጠረው 34 የላሊጋ ጎሎችን የማሳደግ አጋጣሚን ሊፈጥርለት ይችላል።

ሜሲን በቅርብ ርቀት ላይ ሲከተለው የነበረው ሞ ሳላህ ሊቨርፑል ብራይተንን 4-0 ሲያሸንፍ አንድ ጎል በማስቆጠሩ የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ በ 38 ጨዋታዎች 32 ጎሎችን በማስቆጠር ሪከርድ ቢሰብርም በአውሮፓ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ግን በሜሲ ተቀድሟል።

በሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ደግሞ ሀሪ ኬን ሲሆን 30 የሊግ ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።ጉዳት ላይ የሚገኘው ቺሮ ኢሞቢሊ እና ሌዋንዶውስኪ እንዲሁ 29 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ሜሲ የዘንድሮ እንቅስቃሴው በጥልቀት ወደ ኋላ በመመለስ ብዙ ጊዜውን ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ በመሆን እንደ አማካይ እየተጫወተ የአውሮፓ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቁ አስገራሚ ሆኗል።

ሜሲ አብዛኛው የተጫወተበት የሜዳ ክልል [ቀይ ምስል]

ከቡድኑ ባርሴሎና ጋርም ምንም እንኳን ሳይጠበቅ በቻምፕየንስ ሊጉ በሮማ ተሸንፈው ከውድድሩ ውጪ ቢሆኑም በላሊጋው ሁለት ዋንጫዎችን በማንሳት አጠናቋል።

በተለይ የላሊጋ ውድድሩን ሽንፈት ሳይቀምሱ ለማጠናቀቅ ሁለት ጨዋታዎች በቀሩት ውድድር ከሌቫንቴ እና ከሪያል ሶሴዳድ ጋር ከሽንፈት ውጪ ጨዋታቸውን ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል።

Advertisements