ማንችስተር ዩናይትድ ከረዳት አሰልጣኙ ሩይ ፋሪያ ጋር እንደሚለያይ አሳወቀ

ከጆሴ ሞሪንሆ ጋር ላለፉት 17 አመታት ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት ሩይ ፋሪያ ከውድድር አመቱ ፍፃሜ በኋላ ከ ማንችስተር ዩናይትድ ጋር እንደሚለያዩ ክለቡ አሳውቋል።

ሩይ ፋሪያ ጆሴ በረገጡበት ክለብ ሁሉ አብረዋቸው በመጓዝ ላለፉት 17 አመታትን በፖርቶ፣በቼልሲ፣በኢንተር ሚላን፣ማድሪድ እና በማን ዩናይትድ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል።

ነገርግን የሁለቱ አሰልጣኞች የአብሮነት ቆይታ ዩናይትድ ቼልሲን ከሚገጥምበት የኤፍ ኤ ካፕ የዋንጫ ጨዋታ በኋላ ፍፃሜውን ያገኛል።

ጆሴ ” 17 አመት በለይራ፣ፖርቶ፣ለንደን፣ሚላን፣ማድሪድ፣ለንደን በድጋሜ እና ማንችስተር አብረን ልምምድበማሰራት፣በመጫወት፣በመጓዝ፣በመማር፣በመሳቅ እንዲሁም ጥቂት የደስታ እንባዎችን በማፍሰስ በአንድ ላይ አሳልፈናል።ታታሪው ተማሪ አሁን ባለሙያ ሆኗል፣በአሰልጣኝነት ውጤታማ ለመሆን ተዘጋጅቷል።

“ጓደኛዬ ይናፍቀኛል ያ ደግሞ ለኔ ከባዱ ነገር ነው ነገርግን የሱ ደስታ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ውሳኔውን አከብራለው።ምክንያቱም ሁልጊዜ አብረን እንደሆንን አውቃለው፣ደስተኛ ሁን ወንድሜ!” በማለት ጆሴ የጓደኛቸውን መለየት ገልፀውታል።

ሩይ ፋሪያም በዩናይትድ ድረገፅ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ” ከብዙ ሀሳብ በኋላ የምሄድበት ጊዜ እንደሆነ ተሰምቶኛል።ለ17 አመታት የማይረሱ አስደናቂ አመታት ልምድ አግኝቻለው።በአዲስ መንገድ ስራዬን ከመቀጠሌ በፊት ከቤተሰቦቼ ጋር ጥቂት ያማሩ ጊዜያትን ማሳለፍ እፈልጋለው።

“ላለፉት ረጅም አመታት እምነቱ እኔ ላይ ላደረበት ለጆሴ ሞሪንሆ ልዩ ምስጋናዬን አቀርባለው፣እድሉን፣በራስ መተማመኑን፣እውቀቱን እና ልምዱን ከዛ በላይ ደግሞ ጓደኝነቱን ስለሰጠኝ አመሰግናለው።”በማለት ጆሴን አመስግነዋል።

ሩይ ፋሪያ ቀጣይ ክለባቸው ለጊዜው የቱ እንደሆነ ባይታወቅም ምናልባትም የአርሴን ዌንገር ቦታን ለመረከብ ከታጩት አሰልጣኞች ውስጥ አንዱ መሆናቸው የሁኔታዎች መገጣጠም በተለየ መልኩ ጥርጣሬን አሳድረዋል።