ሪከርድ / ሞ ሳላህ የፕሪምየርሊጉን የጎል ሪከርድ ሰበረ

የሊቨርፑሉ አጥቂ ግብፃዊው ሞሀመድ ሳላህ ላለፉት አመታት በአንድ የውድድር አመት በ 38 ጨዋታዎች ተይዞ የነበረውን የከፍተኛ ጎል አግቢነትን ሪከርድ ሰበረ።

የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች በእኩል ሰአት በተለያዩ ሜዳዎች ተካሂዶ ተጠናቋል።

በውድድር አመቱ አስደናቂ አቋሙን በማሳየት የተለያዩ ሽልማቶችን እያገኘ የሚገኘው ሞ ሳላህ ብራይተን ላይ አንድ ጎል ካስቆጠረ በኋላ በፕሪምየርሊጉ 32ኛ ጎሉ ሆኖ ተመዝግቦለታል።

ይህ ጎል ደግሞ ፕሪምየርሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ጀምሮ በአንድ የውድድር አመት በተደረጉ 38 ጨዋታዎች የተቆጠረ ከፍተኛው ጎል በመሆን ከዚህ ቀደም በሶስት ተጫዋቾች ተይዞ የነበረው የ 31 ጎሎች ሪከርድ እንዲሰብር አስችሎታል።

ከዚህ ቀደም ይህንን ሪከርድ በጋራ በአንድ አመት 31 ጎሎችን ይዘው ማጠናቀቅ ችለው የነበሩት በ 1995/1996 ለብላክበርን ሲጫወት የነበረው አለን ሺረር፣2007/2008 ላይ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እንዲሁም 2013/2014 ላይ ልዊስ ስዋሬዝ ነበሩ።

ነገርግን የፕሪምየርሊግ ጨዋታዎች 42 በነበሩበት ጊዜ 34 ጎሎችን በማስቆጠር አለን ሺረር እና አንዲ ኮል በጋራነት የያዙት ሪከርድ አሁንም በሪከርድነት የሚቀጥል ይሆናል።