ማሲሚላኖ አሌግሪ፡ ጁቬንቱስ እስካላሰናበተኝ ድረስ በክለቡ እቆያለሁ

በብዙ ክለቦች ተፈላጊ የሆኑት የጁቬንቱሱ ዋና አሰልጣኝ ማሲሚላኖ አሌግሪ በጣሊያኑ ሻምፒዮን የማይሰናበቱ ከሆነ በቱሪን እንደሚቆዩ ገልፀዋል።

ከሁለቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች፣ አርሰናል እና ቼልሲ እንዲሁም ከሊግ 1 ሻምፒዮኑ ፒኤስጂ የአስጣልኝነት ዝውውር ጋር ስማቸው የተያያዘው ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ትናንት (እሁድ) ምሽት ጁቬን በተከታታይ ለሰባተኛ ጊዜ የስኩዴቶው ሻምፒዮን እንዲሆን ማድረግ ችለዋል።

ከሮማ ጋር ያለግብ በአቻ ውጤት የተለያዩት ጆቬዎች አርሰን ቬንገር ከአርሰናል፣ ኡናይ ኤምሬ ከፒኤስጂ እንደሚለቁ ከተገለፀበት እንዲሁም የአንቶኒዮ ኮንቴ የቼልሲ ቆይታ እርግጥ ባልሆነበት በአሁኑ ጊዜ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው መነጋገሪያ ጉዳይ የሆነው አሌግሪ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ የሴሪ አውን ዋንጫ እንዲያነሱ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ አሌግሪ “የማያሰናብቱኝ ከሆነ በሚቀጥለው ዓመትም በጁቬ እቆያለሁ።” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የቀድሞው የኤሲሚላን አሰልጣኝ አሌግሪ የጣሊያኑን ሻምፒዮን አንቶኒዮ ኮንቴን ተክተው ወደጁቬንቱስ የተዛወሩት በ2014 ነበር።

የ50 ዓመቱ ሰው ከአራት ዓመታት በፊት ክለቡን ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶም ጁቬን ለሁለት ጊዜያት ያህል ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ከማብቃታቸውም ባሻገር አራት የጣሊያን ዋንጫዎችን እና አንድ የጣሊያን ሱፐር ካፕ ዋንጫን ማንሳት ችለዋል።