ሹመት / ፒ ኤስ ጂ ቶማስ ቱሼልን አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩን ይፋ አደረገ

የሊግ ኣ ሻምፕዮኑ ፓሪስ ሴንት ጄርሜይን ኡናይ ኤምሬን በመተካት የቀድሞ የቦሩሲያ ዶርትሙንዱ ቶማስ ቱሼልን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩ አሳውቋል።

ባለፈው ግንቦት 2017 ላይ ከጀርመኑ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ጋር ከተለያዩ በኋላ ስራ ያልነበራቸው ቶማስ ቱሼል የፓሪሱን ሀያል ክለብ በአሰልጣኝነት ለሁለት አመት ተረክበዋል።

የ 44 አመቱ ቱሼል በዶርትሙንድ የርገን ክሎፕን በመተካት ለሁለት አመት ከቆዩ በኋላ መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን ወደ ፔዤ የማቅናት ሰፊ እድል እንዳላቸው ሲነገር ቆይቷል።

ስፔናዊው ኡናይ ኤምሬ በፔዤ የሶስትዮሽ አሸናፊ ቢሆኑም በክለቡ ባለቤቶች በጥብቅ የሚፈለገውን የአውሮፖ ቻምፕየንስ ሊግ ውጤታማ መሆን ባለመቻላቸው የሁለት አመት ኮንትራታቸው ሳይራዘም ቀርቷል።

ቱሼል መረጃው የፔዤ አሰልጣኝ መሆናቸው ይፋ ከሆነ በኋላ “የዚህ ትልቅ ክለብ አሰልጣኝ በመሆኔ ኩራት ተሰምቶኛል።ከነዚህ ትላልቅ ተጫዋቾች ጋር አብሬ እስክሰራ ድረስ ቸኩያለው።ሁሉም የአለማችን ምርጥ ተጫዋቾች ናቸው።

“ከቡድኑ ስታፎች ጋር በመሆን ቡድኑን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ የቻልነውን ያህል እንሰራለን።” ሲሉ ተናግረዋል።

የፔዤው ፕሬዝዳንት ናስር አል ከላይፋ በበኩላቸው “ቶማስ አውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ በቅርቡ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ካሉ አንዱ ምርጥ አሰልጣኝ ናቸው።በግሉ ያለው ባህሪ፣የማጥቃት እንቅስቃሴው በፔዤ ሁልጊዜ የምንፈልገው ነው።” ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

Advertisements