ኦክስሌድ-ቻምብርሌን እስከህዳር ወር ድረስ ከሜዳ ይርቃል

የሊቨርፑሉ አማካኝ አሌክስ ኦክስሌድ-ቻምበርሌን በጉልበቱ ላይ የቀዶ ጥገና እያደረገ መሆኑን ተከትሎ እስከህዳር ወር ድረስ ወደሜዳ አይመለስም።

እንግሊዛዊው ተጫዋች የክረምቱ የዓለም ዋንጫ የሚያመልጠው መሆኑ እርግጥ ቢሆንም፣ ነገር ግን ከዚያም ባለፈ የ2018-19 የውድድር ዘመን የሶስት ወራት ጨዋታዎችም ሊያመልጡት ይችላሉ።

ኦክስሌድ ቻምበርሌን የጉልበት ስር ጉዳት የገጠመው ሊቨርፑል ከሮማ ጋር ባደረገው የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ነበር።

የ24 ዓመቱ ተጫዋች ስኬታማ የቀዶ ህክምና እስኪያገኝ ድረስ ተደጋጋሚ የቀዶ ህክምናዎች እየተደረገለት የሚገኝ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜያትም ከሜዳ ርቆ የሚቆይ ይሆናል።

ባለፈው ክረምት በ40 ሚሊዮን ፓውንድ ከአርሰናል ቀዮቹን የተቀላቀለው ኦክስሌድ-ቻምበርሌን ከጉዳቱ በፊት በሁሉም ውድድሮች ላይ አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍና ስምንት የግብ ዕድሎችን በመፍጠርም ቀዮቹ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ እና በፕሪሚየር ሊጉ የበላይ አራት ደረጃ ውስጥ ገብተው እንዲያጠናቅቁ የራሱን አገዛ ማድረግ ችሏል።

ቀዮቹ በመጪው ክረምት ናቢ ኪየታን ከሬድ ቡል ሌፕዢግ ለማስፈረም ከስምምነት ላይ የደረሱት ያለፈው ነሃሴ ወር ነበር።

በዚህ የውድድር ዘመን 39 ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ የቻለው ኪየታ በይፋ ወደአንፊልድ መዛወር የሚችለው ኃምሌ 1 ቢሆንም፣ ሌላው የሊቨርፑል አማካኝ ኤምሬ ቻን ግን ክለቡን ለመልቀቅ ከጫፍ መድረሱንና የተጫዋቹን ፊርማ የሚያገኘው ክለብ ደግሞ ጁቬንቱስ ሳይሆን እንደማይቀር ዘገባዎች አመልክተዋል።

Advertisements