የባርሴሎና የላሊጋ ያለመሸነፍ ሩጫ ባልታሰበው ሌቫንቴ ተገታ

ሊዮ ሜሲን አሳርፎ ወደ ሜዳ የገባው ባርሴሎና ሳይሸነፍ ላሊጋውን ለማጠናቀቅ ሲያደርግ የነበረው ሩጫ በ 37ኛው ሳምንት 16ኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ሌቫንቴ ተሸንፎ ፍፃሜውን አግኝቷል። 

37ኛ ሳምንት የስፔን ላሊጋ ጨዋታ የባርሴሎና ደጋፊዎችን አንገት ያስደፋ እንዲሁም ያልታሰበ ሪከርድ ለሰበሩት የሌቫንቴ ተጫዋቾችን ያስፈነጠዘ ውጤት ተመዝግቧል።

ጋናዊው ኢማኑኤል ቦአቴንግ በደመቀበት ምሽት ሌቫንቴ ባርሴሎናን 5-4 በማሸነፍ የካታላኑ ቡድን ሽንፈት ሳይቀምስ ላሊጋውን የማጠናቀቅ እድሉ ላይ ውሀ ቸልሶበታል።

ሌቫንቴዎች ፍፁም ደካማ በነበረው የባርሴሎና ተከላካይ ላይ እንደፈለጉ እየፈነጩ ሳይቸገሩ አምስት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ለእረፍት ወደ መልበሻ ቤት ከማቅናታቸው ቀደም ብሎ ባርሴሎና በኮቲንሆ አማካኝነት ተስፋ የሰጠችውን ጎል አስቆጥሮ በባለሜዳዎቹ 2-1 መሪነት ለእረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት መልስ እብደት በታየበት እንቅስቃሴ ሌቫንቴ ደካማ የነበረውን የፒኬ እና የየሪ ሜና ጥምረት በፈጣን መልሶ ማጥቃት በመሰባበር አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች ጨዋታውን 5-1 መምራት ችለው ነበር።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ብዙም ያልተቸገሩት ባርሴሎናዎች በበኩላቸው ኮቲንሆ ባስቆጠራቸው የሀትሪክ ጎሎች እንዲሁም የስዋሬዝ የ 71ኛ ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅመው ጨዋታውን ወደ 5-4 ወስደውት ነበር።

አቻ ለመሆንም ይሁን ለማሸነፍ በቂ ጊዜ አግኝተው የነበሩት እንግዳዎቹ ባርሴሎናዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ለማግባት ያደረጉት ጥረት በሌቫንቴዎች ብርቱ የመከላከል ብቃት እና ብልጠት የታከለበት የሰአት የማባከን እንቅስቃሴ ሳይሳካላቸው ተሸንፈዋል።

ሽንፈቱ ለባርሴሎና የአመቱ የመጀመሪያው ቢሆንም ቀላል በነበረው ጨዋታ እና ላሊጋውን ያለሽንፈት ሊያጠናቅቅ የሚችልበት ሰፊ እድሉን 37ኛ ሳምንት ላይ አበላሽቶታል።

በአጠቃላይ ባርሴሎና ከ 43 የላሊጋ ጨዋታ በኋላ መሸነፍ የቻለ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ የተሸነፈው መጋቢት 2017 በማላጋ ነበር።

2003 ላይ ማላጋ አምስት ጎሎችን ካስቆጠረበት በኋላ ባርሴሎና በአንድ ጨዋታም አምስት ጎል ሲያስተናግድ ከ 15 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሆኗል።

ጋናዊው የ 21 አመቱ ኢማኑኤል ቦአቴንግ ባርሴሎና ላይ ሀትሪክ የሰራው ደግሞ 2005 ላይ ለቪላሪያል ሲጫወት ከነበረው ከዲያጎ ፎርላን በኋላ ለመጀመሪያ ነው።

ከጨዋታው በኋላ የቡድኑ አሰልጣኝ ቫልቬርዴ ላይ ትችቶች ቀርበዋል።በተለይ ለሜሲ እረፍት ሰጥተው ወደ ቫሌንሺያ ማቅናታቸው በጨዋታው ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል።

ምክንያቱም ቡድናቸው በሜሲ ጥገኛ አድርገው በመገንባታቸው እሱ በማይኖር ጊዜ ባርሴሎና ተራ ቡድን ሆኖ መታየቱ ነው።

Advertisements