የኡመድ ኡኩሪው ሰሞሃ በግብፅ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ለሁለተኛ ጊዜ በዛማሌክ ተሸነፈ

ምሽት ላይ በአሌክሳንድሪያ ቦርግአረብ ስታድየም በኢትዮጵያዊው ኡመድ ኡኩሪ አጥቂነት የሚመራው የግብፁ ሰሞሃ በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ በግብፅ ዋንጫ ለፍፃሜ ቢጫወትም እንደ 2014 ቱ ሁሉ በድጋሚ በዛማሌክ ተሸንፎ ዋንጫውን ሳያገኝ ቀርቷል።

ሰሞሃ 2014 ላይ በተመሳሳይ ለፍፃሜ ቀርቦ በአሁኑ ተፋላሚው ዛማሌክ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ተሸንፎ ዋንጫውን ማግኘት ሳይችል ቢቀርም በድጋሚ ዘንድሮ ሁለቱ ቡድኖች በመገናኘታቸው የ 2014 ቱን የፍፃሜ ጨዋታ መበቀል የሚችልበት መልካም አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ኡመድ በአጥቂነት በተሰለፈበት ጨዋታ ላይ ሰሞሃ ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ጎል ገና ጨዋታው ከመጀመሩ በአምስተኛው ደቂቃ በሆሳም ሀሰን አማካኝነት አስቆጥረው እስከ 86ኛው ደቂቃ ድረስ መምራት ችለው ነበር።

በጨዋታው የሰሞሃው ጎል አስቆጣሪ የነበረው ሆሳም ሀሰን በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ ዛማሌኮች ተጭነው ለመጫወት ሲሞክሩ ሰሞሃዎች ደግሞ ውጤቱን ለማስጠበቅ ሲጥሩ ታይተዋል።

አሰልጣኙም እስከ 79ኛው ደቂቃ ድረስ ሜዳ ላይ የነበረው ኡመድ ኡኩሪን ቀይረው አስወጥተው የተከላካይ ተጫዋች ቀይረው አስገብተዋል።

ነገርግን የዲ ሪ ኮንጎው ተጫዋች የሆነው ካቦንጎ ኪሶንጎ 86ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል ጨዋታው በሙሉ የጨዋታ ጊዜ 1-1 እንዲጠናቀቅ አድርጎ ወደ ጭማሪ ሰአት እንዲያቀና አድርጎታል።

በጭማሪ ሰአትም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጎል ባለመቆጠሩ ወደ መለያ ምት አቅንተዋል።የሰሞሃው ተከላካይ አብዱላህ ባክሪም የመጀመሪያውን ኳስ መጠቀም ባለመቻሉ ዛማሌኮች የዋንጫ ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ኡመድ ኡኩሪ

ዛማሌክ ይህን ዋንጫ ሲያነሳ ለ 26ኛ ጊዜው ሲሆን ከ2013 እስከ 2016 ድረስ በተከታታይ አሸናፊ ሆኗል።2017 ላይ አል አህሊ ቢያሸንፍም በድጋሚ 2018 ላይ ዛማሌክ የአሸናፊ ክብሩን መልሶ አግኝቶታል።

ሰሞሃ በበኩሉ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫውን ባለቤት ለመሆን ያደረገው ጥረት ለሁለተኛ ጊዜ ተበላሽቶበታል።

ቡድኑ 2014 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍፃሜ ቀርቦ በተመሳሳይ በዛማሌክ ተሸንፎ ዋንጫ ማጣቱ የሚታወስ ሲሆን ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪም ከሰሞሃ ጋር ዋንጫ የማንሳት እድሉ ተበላሽቶበታል።

በተለይ ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በትኩረት ማነስ የሚያስተናግዳቸው ጎሎች ዋጋ እያስከፈሉት እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

ዛማሌክ የግብፅ ዋንጫን በማሸነፉ የዘንድሮ የግብፅ ፕሪምየርሊግ ካሸነፈው አል አህሊ ጋር በአሸናፊዎች አሸናፊ የሚፋጠጡ ይሆናል።

ዛማሌክ የአሸናፊዎች አሸናፊን ለሶስት ጊዜ ባለድል ሲሆን አል አህሊ ደግሞ ለአስር ጊዜ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።