የግብፁ አል አህሊው አሰልጣኝ ሆሳም ኤል ባድሪ ከሀላፊነታቸው በፈቃዳቸው ለቀቁ

በካፍ ቻምፕየንስ ሊግ የምድባቸውን ሁለተኛ ጨዋታ ወደ ካምፓላ በማቅናት ወደ ምድብ ድልድሉ ቅ/ጊዮርጊስን በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በገባው ኬሲሲኤ የተሸነፈው የግብፁ አል አህሊ አሰልጣኝ ሆሳም ኤል ባድሪ ከሽንፈቱ በኋላ በፈቃዳቸው ከሀላፊነታቸው ለቀዋል።

<!–more–>

40 ጊዜ የግብፅ ፕሪምየርሊግ እንዲሁም ስምንት ጊዜ የካፍ ቻምፕየንስ ሊግ አሸናፊው አል አህሊ ወደ ዩጋንዳ አቅንቶ ከ ኬሲሲኤ ጋር ያደረገው የቻምፕየንስ ሊግ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ተሸንፏል።

ኬሲሲኤ የኢትዮጵያውን ቅ/ጊዮርጊስን በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ካፍ ቻምፕየንስ ሊግ የምድብ ድልድል የገባ ሲሆን በሜዳው ያደረገውን ጨዋታ አህሊን ማሸነፉ አስገራሚ አድርጎታል።

በተቃራኒው ደግሞ ሽንፈቱ ከመጀመሪያው የምድቡ የሜዳው ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ ይዞ ለመጣው እና የውድድሩ ከፍተኛ ልምድ ባለቤት አህሊ አስደንጋጭ ሽንፈት ሆኗል።

ይህም ውጤት የቡድኑ አሰልጣኝ ሆሳም ኤል ባድሪ በራሳቸው ፈቃድ ከሀላፊነታቸው እንዲለቁ አስገድዷቸዋል።ጥያቄያቸውን በክለቡ ተቀባይነት እንዳገኘ ታውቋል።በምትካቸውም ረዳት አሰልጣኙ አህመድ አዩብን ጊዚያዊ አሰልጣኝ አድርገው ቀጥረዋል።

ቦርዱ ዛሬ ስለ ክለቡ ቀጣይ አሰልጣኝ ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርግም በድረገፁ ላይ አሳውቋል።

አሰልጣኙ ለሁለት አመታት ቡድኑን የመሩ ሲሆን ሁለት የሊግ ዋንጫዎችን እና አንድ የግብፅ ዋንጫን አሸንፈዋል።የ2017 የካፍ ቻምፕየንስ ሊግንም ለፍፃሜ መድረስ ችለዋል። 

ቡድኑ ከሁለት የቻምፕየንስ ሊግ ጨዋታዎች ውስጥ ማግኘት የቻለው አንድ ነጥብ ብቻ ሲሆን እሱም ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ ጋር በሜዳው ተጫውቶ ያለግብ የተጠናቀቀው ጨዋታ ነው።በምድቡም የጨረሻውን ደረጃ ይዟል።

አህሊ ምንም እንኳን የግብፅ ፕሪምየርሊግን ቀደም ብሎ አሸናፊ መሆኑን ቢያረጋግጥም በሊጉ በዛማሌክ 2-1 ከተሸነፈ በኋላ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

በግብፅ ዋንጫም በአላሲዮቲ ስፖርት ክለብ ከሁለት ሳምንት በፊት ተሸንፎ ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ ሳይችል መቅረቱ ይታወሳል።

በዘንድሮ የካፍ ቻምፕየንስ ሊግ የዋንጫ ባለቤት 2.5 ሚሊየን ዶላር የሚሸለም ሲሆን ሁለተኛ የሚወጣው ደግሞ 1.25 ሚሊየን ዶላር ያገኛል።

Advertisements