ስኬት / የጣሊያኑ ፓርማ ከሶስት አስደናቂ አመታት በኋላ ወደ ሴሪ ኣው ተመለሰ

2015 ላይ ለተጫዋቾቹ ደሞዝ መክፈል እንኳን ተቸግሮ በኪሳራ ወደ ሴሪ ዲ ወርዶ የነበረው የጣሊያኑ ፓርማ ከሶስት ተከታታይ ስኬታማ አመታት በኋላ ከሴሪ ዲ ጀምሮ እያደገ በመምጣት ወደ ጣሊያን ሴሪ ኣው መመለሱ አረጋግጧል።

1990ዎቹ ውስጥ ከጣሊያን አልፎ በአውሮፓ ስመ ገናና የነበረው ፓርማ ባለፉት ሶስት አመታት ስሙ ተዳፍኖ ቆይቷል።

ቡድኑ 2015 ላይ በገንዘብ እጥረት ኪሳራ ውስጥ ገብቶ በሴሪ ኣው ለመወዳደር አቅም በማጣቱ ወደ ሀገሪቷ አራተኛ እርከን ላይ ወደሚገኘው  ወደ ሴሪ ዲ ለመውረድ ተገዶ ነበር።

በወቅቱ ለተጫዋቾች ደሞዝ ለመክፈል ሁሉ ተቸግሮ ነጥብ ተቀንሶበት በሴሪ ኣው መጨረሻ ደረጃ ላይ አጠናቆ ወደ ሴሪ ቢ ቢወርድም ቡድኑ ለጨረታ ቀርቦ ገዢ በማጣቱ ወደ ሴሪ ዲ አሽቆልቁል ወርዶ ነበር።

ነገርግን ከሴሪ ዲ የተነሳው ፓርማ በየአመቱ ውጤታማ በመሆን እና ወደ ሴሪ ሲ፣ሴሪ ቢ እያለ እያደገ መጥቶ ከሶስት ውጤታማ አመታት በኋላ ወደ ሴሪ ኣው መመለሱን አረጋግጧል።

በዚህም ምክንያት ፓርማ በጣሊያን በሶስት ተከታታይ አመታት ወደ ቀጣዩ እርከን በማደግ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል።

ቡድኑ አርብ ምሽት በነበረው ጨዋታ ላይ በሴሪ ቢ በፍሮሲዮኔ ተቀድሞ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የነበረ ቢሆንም ፍሮሲዮኔ ከፎጊያ ጋር 2-2 መለያየቱ እንዲሁም ፓርማ ደግሞ ስፒዚያን 2-0 በማሸነፉ የሊጉን መሪ ኢምፖሊን ተከትሎ ወደ ሴሪ ኣው መመለሱ አረጋግጧል።

ፓርማ በ 1990ዎቹ አማካይ እና መጨረሻ ላይ እንደ ክሪስፖ፣ቱራም፣ካናቫሮ፣ኤነሪኮ ቼይዛ፣ቡፎንየመሳሰሉት ኮከብ ተጫዋቾች የተጫወቱበት ታላቅ ቡድን የነበረ ሲሆን ምንም እንኳን የሴሪ ኣ ዋንጫ ባያነሳም ከ 1992 እስከ 2002 ሰባት ዋንጫዎችን አሸንፏል።ከነዚህ ውስጥ ሁለት የአውሮፓ ማህበረሰብ ዋንጫ ይገኝበታል።

Advertisements