ቼልሲ ኮንቴን ከማሰናበቱ በፊት “ሶስት ጊዜ” ማሰብ እንዳለበተ ቪያሊ ተናገረ

የቀድሞው የቼልሲ የተጫዋች-አሰልጣኝ ጂያንሉካ ቪያሊ ቼልሲ በአንቶኒዮ ኮንቴ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ተቻኩሎ ከውሳኔ ላይ እንዳይደርስ አሳስቧል።

ሰማያዊዎቹ ቅዳሜ ከማንችስተር ዩይትድ ጋር የሚያደረጉት የኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ ለአንቶኒዮ ኮንቴ በክለቡ የመጨረሻቸው እንደሚሆን የሚገልፁ የጭምጭምታ ወሬዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ቼልሲ በፕሪሚየር ሊጉ በአምስተኛ ደረጃ መጨረሱን ተከትሎ በርካታ ዘገባዎች በኮንቴና በክለቡ መካከል ውጥረት መፈጠሩን እና አሰልጣኙ ከቀጣዩ የውድድር ዘመን በፊት ክለቡን እንደመለቁ አመላክተዋል።

ይሁን እንጂ ቪላ ስለአሰልጣኙ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከመወሰናቸው በፊት ሁለቱም አካላት በጥንቃቄ ሊያስቡበት እንደሚገባ ሃሳቡን ሰጥቷል።

“እኔ አንቶኒዮ [ኮንቴ]ን ብሆን ቼልሲን ከመልቃቄ በፊት ሁለት ጊዜ አባለሁ።” ሲል ቪያሊ ለስካይ ስፖርትስ ኒውስ ተናግሮ “ቼልሲን ብሆን ደግሞ አንቶኒዮን [ኮንቴ] እንዲሄድ ከማድረጌ በፊት ሶስት ጊዜ አስብበታለሁ።” በማለት ጨምሮ ተናግሯል።

“ባለፈው የውድድር ዘመን ስድስትና ሰባት ተፎካካሪ ባሉትና ለመፎካከር የሚከብደውን ሻምፒዮንሺፑን [ፕሪሚየር ሊጉን] በማሸነፍ በሚደንቅ ሁኔታ ጥሩ ነገር ሰርቷል ብዬ አስባለሁ። ውድድሩ በሚገርም ሁኔታ ከባድ ነው። ነገር ግን እሱ በታላቅ ክብር አሳክቶታል።”

“ሻምፒዮንሺፑን ባሸነፍክ ማግስት ያለው የውድድር ዘመን ሁልጊዜም ይበልጥ አቸጋሪ ይሆናል። ፉክክሩም እየከበደና እየጠነከረ ይመጣል። ስለዚህ እሱ በዚህ የውድድር ዘመን የሚችለውን ሁሉ አድርጓል ብዬ አስባለሁ።

“በሻምፒዮንስ ሊጉ እኔ ባርሴሎና ሳይሆን መሲ አስወጣቸው ብዬ በማስበው ክለብ ከውድድሩ ውጪ እስኪሆኑ ድረስ ፍፁም ጥሩ ነገር ማድረግ ችለው ነበር። እሱ [መሲ] የተጫወተው ለቼልሲ ቢሆን ኖሮ በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ቼልሲ 5ለ0 ያሸንፍ ነበር።

“ለኤፍኤ ዋንጫው ፍፃሜ መድረስም ትልቅ ስኬት ነው። ስለዚህ በአጠቃላይ እሱ [ኮንቴ] ጥሩ ጉዞ እያደረገ ይገኛል። ይህንንም እንደሚቀጥልበት ተስፋ አለኝ።” ሲል ቪያሊ ተናግሯል።