ፊል ጆንስ በሃዛርድ ላይ በፈፀመው ጥፋት ለምን በቀይ ካርድ ከሜዳ አልወጣም?

ጆንስ በኤፍኤው ዋንጫው ፍፃሜ ኤዲን ሃዛርድ ማግባት የሚችለውን ግልፅ የግብ ዕድል ለማጨናገፍ ባደረገው ጥረት ጥፋት በመፈፅሙ ቼልሲ የፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኝ፣ ጆንስ ደግሞ ለጥፋቱ የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል። ይሁን እንጂ ሃዛርድ የመጨረሻ ተጫዋች እንደመሆኑ ጆንስ ቀይ ካርድ አልተመለከትም። ለምን?

የማንችስተር ዩናይትዱ ተከላካይ ለፈፀመው ቅጣት ቢጫ ካርድ ተመልክቶ ከሜዳ ከመሰናበት ተርፏል። ምክኒያቱ ደግሞ በ2016 የወጣው ህግ ነው።

ዓለም አቀፉ የእግርኳስ ማህበር ቦርድ (አይፋብ) ግልፅ የሆነ የማግባት ዕድልን በሚፈፅሙት ጥፋት ያጨናገፉ ተጫዋቾች በቀጥታ ከሜዳ የሚያሰናብተውን የቀድሞ ህግ ቀይሮታል።

እንደጆንስ አይነት ኳስን ለመጫወት ጥረት በማድረግ ላይ ሳሉ “በድንገተኛ ስህተት ጥፋት የሚፈፅሙ” ተጫዋቾች ቀይ ካርድ መመልከት እንደማይገባቸውም አዲሱ የአይፋብ ህግ ደንግጓል።

አዲሱን ህግ ያወጣው ዓለም አቀፉ የእግርኳስ ማህበር የቀድሞውን ግብ የማስቆጠር ዕድል ማጨናገፍን ለማስተካክል ምክኒያት ሆኖኛል ያለው ደግሞ ጥፋት ፈፃሚው ቡድን ለ”ሶስት ዓይነት ቅጣት” እንዳይዳረግ በማሰብ ነው። ይኸውም ፍፁም ቅጣት ምት፣ ተጫዋችን ከሜዳ ማጠትና ምናልባትም የፍፁም ቅጣት ምቱ ከተቆጠረ ግብ ማስተናገድን በአንድ ጊዜ እንዳይፈፀም ለማስቀረት ነው።

ይሁን እንጂ ሆን ብሎ የተፈፀመ ጥፋት ከሆነ ግን የቀድሞው ህግ ለጥፋት ፈፃሚው ተጫዋችም ሆነ ለቡድኑ ርህራሄ እንደሌለው አዲሱ ህግ በግልፅ አስፍሯል። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነው ሎረን ኮሺየልኒ በሮበርት ሊቫንዶውስኪ ላይ ፈፅሞት የነበረው ጥፋት አይነት ነው።