ሹመት : ማኑኤል ፔሊግሪኒ የዌስትሀም ዩናይትድ አሰልጣኝ በመሆን ወደ እንግሊዝ ተመለሱ 

የቀድሞ የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ የነበሩት ማኑኤል ፔሊግሪኒ በድጋሚ ወደ እንግሊዝ በመመለስ የለንደኑን ዌስትሀም ዩናይትድ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል።

ቺሊያዊው ፔሌግሪኒ የቻይና ሱፐርሊግ ተሳታፊ የሆነው ሂቤይ ቻይና ፎርቹን ሲያሰለጥኑ ከቆዩ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ከክለቡ ጋር መለያየታቸው ይታወሳል።

ዌስትሀም በበኩሉ ዴቪድ ሞይስን ካሰናበተ በኋላ ከፔሊግሪኒ ጋር ስሙ ሲያያዝ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም አሰልጣኙን ለሶስት አመት የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩ አሳውቋል።

የመዶሾቹ ሊቀመንበር ዴቪድ ሲሊቫን በአዲሱ አሰልጣኝ ዙሪያ ሲናገሩ “ማኑኤል ፔሌግሪኒን ወደ ክለባችን እንኳን ደህና መጣህ ማለት እወዳለው።

“እሱ በአለማችን ካሉ የተከበሩ አሰልጣኞች ውስጥ አንዱ ነው።ከሱ ጋር ለመስራትም ተዘጋጅተናል።

“የፕሪምየርሊጉ ልምድ እና እውቀት ያለው አሰልጣኝ መቅጠራችን በጣም ጥሩ ነገር ነው።” ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞ የቪላሪያል፣ማድሪድ እና ማላጋ አሰልጣኝ የነበሩት ፔሊግሪኒ ከማን ሲቲ ከተለያዩ ከሁለት አመት በኋላ ወደ እንግሊዝ መመለስ የቻሉ ሲሆን በ 2013/2014 ላይ ከሲቲ ጋር የፕሪምየርሊግን ዋንጫ ማሸነፋቸው ይታወሳል።

Advertisements