አርሰናል በመጨረሻ ፊቱን ወደ ኡናይ ኤምሪ አዞረ

የአርሰናል ቦርድ ለክለቡ አሰልጣኝነት አርቴታን ለመቅጠር ጫፍ ላይ ከደረሰ በኋላ በአስራ አንደኛው ሰአት ላይ እይታውን ወደ ስፔኑ ኡናይ ኤምሪ ማድረጉ ታውቋል።

የመድፈኞቹን የረጅም ጊዜ አለቃ የነበሩትን አርሴን ዌንገር ለመተካት ስራ የበዛበት የአርሴናል ቦርድ ቀጣዩን አሰልጣኝ ለማግኘት አማራጮችን እየተመለከተ ይገኛል።

ቀደም ብሎ አሌግሪ፣ኤነሪኬ እና አርቴታ ክለቡን ለማሰልጠን እንደሚፎካከሩ ቢነገርም ቀስበቀስ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በተለያዩ ምክንያቶች ክለቡን እንደማይረከቡ ከታወቀ በኋላ አርቴታ አዲሱ የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ለመሆን መቃረቡ ተነግሮ ነበር።

አርቴታ ባለፈው  አርብ ከቡድኑ ጋር በአዲሱ ሀላፊነቱ ዙሪያ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላፐ ለ 3 አመታት በየአመቱ 4 ሚሊየን ፓውንድ እየተከፈለው ቡድኑን እንዲያሰለጥን በመርህ ደረጃ ተስማምተው ነበር።

ነገርግን አርቴታ ሰፊ የማሰልጠን ልምድ የሌለው በመሆኑ የአርሰናል የአሰልጣኝነት ቦታ ሊከብደው እንደሚችል በማሰብ ከሹመቱ በፊት የተቃወሙ ብዙ ደጋፊዎች ነበሩ።

ቦርዱ አሁን ይህን የደጋፊዎች ስጋት የተጋራው ይመስላል፤በአስራ አንደኛው ሰአት ላይ አርቴታን ወደ ጎን በመተው ስፔናዊ   ኡናይ ኤምሪን ለመቅጠር ከጫፍ ቆሟል።

ኡናይ ኤምሪ ሰኞ ለታ ወደ ለንደን አቅንተው ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኙ በቫሌንሺያ፣ሲቪያ እና በ ፒ ኤስ ጂ ቆይታ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በተለይ በሲቪያ ቆይታቸው ሶስት የዩሮፖ ሊግ ዋንጫን ማንሳታቸው ይታወሳል።