ክርስቲያኖ ሮናልዶ አንድ ጋዜጠኛን አቆሰለ

ዛሬ ምሽት በኬቭ ለሚደረገው ከቻምፕየንስ ሊጉ የፍፃሜ ጨዋታ በፊት የአርቡን የልምምድ መርሀ ግብር ሲያከናውን የነበረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ አንድ ጋዜጠኛን አቁስሏል።

ምሽት ላይ ተጠባቂው የቻምፕየንስ ሊግ ጨዋታ በሪያል ማድሪድ እና በሊቨርፑል መካከል ይካሄዳል።

ማድሪዶች ለሶስተኛ ተከታታይ አመት የቻምፕየንስ ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት፣ሊቨርፑሎች ደግሞ ከ 2005 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ነው።

ለዚህ ጨዋታ ልምምዳቸውን በኬቭ ኦሎምፒክ ስታድየም እያከናወኑ የነበሩት ማድሪዶች አርብ ለታ ድንገተኛ ያልታሰበ አጋጣሚ በልምምድ ሜዳ ላይ አጋጥሟቸዋል።

በልምምዱ መሀል ላይ የቡድኑ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የመታው ጠንካራ ኳስ ምስል ለማንሳት ሲሰናዳ በነበረ ጋዜጠኛ ቅንድብ አካባቢ አርፎ አቁስሎታል።

ለአሜሪካው የቴሌቭዥን ጣቢያ ለሆነው ዩኒቪዥን ዲፖርትስ ኔትወርክ በስፓኒሽ ቋንቋ የሚሰራው ጋዜጠኛ ሎሬንዛ ፕሪቶ ቅንድቡ ተሰንጥቆ ደም ሲፈሰው የታየ ሲሆን ወዲያውኑ ህክምና ተደርጎለት በፕላስተር ተለጥፎለታል።

ኮከቡ ሮናልዶም ጋዜጠኛውን እጁን በማውለብለብ ይቅርታ ከጠየቀው በኋላ ከልምምዱ በኋላ ለጋዜጠኛው የራሱ የሆነው የሪያል ማድሪድ ጃኬት በስጦታ አበርክቶለታል።

ጋዜጠኛውም በተደረገለት ነገር በመደሰት ጃኬቱን ይዞ ፈገግ በማለት ፎቶ ሲነሳ ተስተውሏል።

ሮናልዶ በሚታወቅበት ጠንካራ ምቱ በምሽቱ የቻምፕየንስ ሊጉ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የሊቨርፑል ግብ ጠባቂን ይፈትን ይሆን?