የሞ ሳላህ ጉዳት ተጫዋቹን ከአለም ዋንጫው ውጪ ያደርገው ይሆን?

ግብፃዊው ሞ ሳላህ ትናንት ምሽት በቻምፕየንስ ሊጉ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ጉዳት አጋጥሞት ከሜዳ ተቀይሮ ወጥቷል።

ተጫዋቹ 31ኛ ደቂቃ ላይ ከሜዳ ከመውጣቱ ቀደም ብሎ ከሰርጂዮ ራሞስ ጋር በነበራቸው ትንቅንቅ ሜዳ ላይ በትከሻው በመውደቅ ጉዳት አጋጥሞታል።

ጉዳቱም ጨዋታውን ለመቀጠል ስላላስቻለው ጨዋታውን እያነባ አቋርጦ ለመውጣት ተገዷል።

ይህ ደግሞ ሊቨርፑሎች የፍፃሜ ጨዋታውን ኮከባቸውን ሳይዙ እንዳሰቡት ሳይሆን በሪያል ማድሪድ በቀላሉ እንዲሸነፉ አድርጓቸዋል።

የተጫዋቹ ጉዳት ለግብፅ ብሔራዊ ቡድንም አስደንጋጭ በመሆኑ ምሽቱን በፈርኦኖቹ ካምፕ ድንጋጤን ፈጥሯል።

ነገርግን ተጫዋቹ ከጨዋታው በኋላ ወደ ሆስፒታል በማቅናት ምርመራ አድርጎ የጉዳቱ መጠን ታውቋል።

የተሰማው ዜናም ሞ ሳላህ ያጋጠው ጉዳት ምንም አይነት የጡንቻ መሰንጠቅ ባለማሳየቱ ለአለም ዋንጫው የመድረስ እድሉ በመልካም ጎኑ እንዲታሰብ የሚያደርግ ነው።

ጭንቀት ውስጥ ገብቶ የነበረው የግብፅ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ምሽት ላይ ያሳወቀው መረጃ መላው ግብፃዊያን ያረጋጋ ሆኗል።

እግርኳስ ማህበሩ የብሔራዊ ቡድኑ ሀኪሞች ከሊቨርፑል ሀኪሞች ባረጋገጡት መረጃ መሰረት ጉዳቱ የጡንቻ መሰንጠቅ እንደሌለው እና ለአለም ዋንጫው መሳተፍ እንደሚችል ነው።

ግብፅ ለአለም ዋንጫው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሰኔ 1 እና ሰኔ 6 ላይ ከኮሎምቢያ እና ከቤልጄም ጋር የምትጫወት ይሆናል። 

በአለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታዋንም በምድብ አንድ ሰኔ 15 ላይ ከኡራጋይ ጋር በማድረግ የምትጀምር ሲሆን በመቀጠልም ከአዘጋጇ ራሺያ እና ሳውዲ አረቢያ ጋር ትጫወታለች።