ውዝግብ: ራሂም ስተርሊንግ እና አወዛጋቢው ታቱው

እንግሊዛዊው የማን ሲቲው የመስመር ተጫዋች የሆነው ራሂም ስተርሊግ ከሰሞኑን እግሩ ላይ የተነቀሰው ታቱ አወዛግቧል።

23ኛ አመቱ ላይ የሚገኘው ስተርሊንግ ከሲቲ ጋር ድንቅ አመትን አሳልፏል።የፔፕ ጓርዲዮላ ወደ ክለቡ መቀላቀል የተጠቀመው አንዱ ተጫዋች እሱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ለክለቡ የፕሪምየርሊግ ድልም ጎሎችን በማስቆጠር እና ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በመስጠት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አድርጓል።

ተጫዋቹ ለአለም ዋንጫ ከሚሳተፈው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጋር ልምምዱን እያከናወነ ቢገኝም ሰሞኑን እግሩ ላይ ተነቅሶ የመጣው ምስል ብዙዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲወያዩ ያስገደደ ነበር።

ስተርሊንግ በቀኝ እግሩ ላይ የጠመንጃ ምስል ያለው ታቱ ተነቅሶ ይታያል።ይህን ምስል ደግሞ በሌላ መንገድ የተረጎሙት አልጠፉም።

ሰላምና ፀጥታ በአለማችን ላይ መስበክ ሲገባ የመሳሪያ ምስልን እየሳሉ ፀጥታን የሚያደፈርስ መልእክት ያለው ምስል ማስተዋወቁ አግባብ አለመሆኑ በመጥቀስ ተጫዋቹ ትክክለኛ ነገር አለማድረጉ በመግለፅ ወቅሰውታል።

በእንግሊዙ ዘሰን ጋዜጣም መረጃውን ይዞት በመውጣት በሰፊው ካራገበው በኋላ ተጫዋቹ ለምን እንደተነቀሰ ምላሽ ለመስጠት ተገዷል።

“አባቴ ሁለት አመቴ ላይ እያለው በጥይት ተገድሎ ሞቷል።ከዛ በኋላ በህይወቴ ጥይት የሚባል ነገር በእጄ ላለመንካት ቃል ገባው።ቀኝ እግሬ ላይም የተነቀስኩት ጥልቅ የሆነ ያላለቀ ሚስጢር ስላለው ነው።” በማለት ስተርሊንግ ስለ ታቱው ምላሽ ሰጥቷል። 

ተጫዋቹ በእጁ ላለመንካት ቃል በመግባቱ ምስሉን በማውገዝ መልክ መጠቀሙ ነው ለመግለፅ የሞከረው።

የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበርም ጉዳዩን በመረዳት ድጋፍ በመስጠት የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ትኩረታቸውን በአለም ዋንጫው ላይ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

እንግሊዝ በአለም ዋንጫው የመጀሪያዋን ጨዋታ ከአፍሪካዊቷ ተወካይ ቱኒዚያ ጋር በማድረግ የምትጀምር መሆኗ ይታወቃል።

Advertisements