የአሰልጣኞች ሹመቶች እና ስንብቶች

ትናንትና በአለማችን የተሰሙ የአሰልጣኞች ሹመቶች እና የስንብት መረጃዎች በአንድ ላይ ተጠቃለው ቀርበዋል።


የቱኒዚያው ሴፋክሰን ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ቀጠረ

ሆላንዳዊው ሩድ ክሮል ለሁለተኛ ጊዜ የቱኒዚያውን ሴፋክሰን አሰልጣኝ ተደርገው ተሹመዋል።

አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም 2012 እና 2013 ላይ ክለቡን በማሰልጠን የሊጉ እና የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አሸናፊ መሆን ችለው ነበር።

በቱኒዚያ የተከበሩት የ69 አመቱ ክሮል ወደ ደ/አፍሪካም በማቅናት ከኦርላንዶ ፓይሬትስ ጋር መልካም ቆይታ አድርገዋል።

ሌላው የሀገሪቷ ክለብ የሆነውን ኤስፔራንስንም ለጥቂት ጊዜ ማሰልጠን ችለው ነበር።


ዚዳን እና ማድሪድ ተለያዩ

ከሶስት አመታት ቆይታ በኋላ ዚዳን ከማድሪድ የአሰልጣኝነት ሀላፊነቱ በፈቃዱ ለቋል።

አሰልጣኙ ለሶስት ተከታታይ አመታትን የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳቱን ካረጋገጠ በኋላ የወሰነው ውሳኔ አስገራሚ ሆኗል።

ለጁቬንቱስ እና ለማድሪድ በተጫዋችነት ማገልገል የቻለው ዚዳን እስከ 2020 ድረስ ኮንትራት ቢኖረውም ክለቡ ለውጥ ያስፈልገዋል በሚል ሀላፊነቱን ለቋል።

ዚዳን ስለ ውሳኔው ሲናገር”ያልተለመደ ውሳኔ እንደሆነ አውቃለው ነገርግን ትክክለኛው ወቅት ነው።ይህ ቡድን እያሸነፈ መቀጠል ያለበት እና ለውጥ የሚያስፈልገው ነው።

“ከሶስት አመታት በኋላ ቡድኑ አዲስ ድምፅ፣አዲስ አቀራረብ እና አዲስ አሰራርን ይፈልጋል።

“ይህንን ክለብ እወደዋለው።ይህን እድል በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ለሰጡኝ የክለቡ ፕሬዝዳንትም እወዳቸዋለው፣ነገርግን ዛሬ ለውጥ ማድረግ አለብን እኔም ውሳኔዬን የወሰንኩት ለዛ ነው።”በማለት ተናግሯል


ፍራንክ ላምፓርድ የደርቢ ካውንቲ አሰልጣኝ ሆነ

የቀድሞ የፕሪምየርሊጉ ተሳታፊ የነበረው ደርቢ ካውንቲ የቀድሞውን የቼልሲ አማካይ የነበረውን ፍራንክ ላምፓርድን በአሰልጣኝነት ቀጥሯል።

ላምፓርድ 20 አሰልጣኞች በእጩነት በቀረቡበት የደርቢ የአሰልጣኝነት ክፍት የስራ ቦታ ላይ ቅድሚያውን በማግኘት ለሶስት አመታት ኮንትራቱን ፈርሟል።

ጋሪ ሮውሌትን ተክቶ ወደ ደርቢ ያቀናው ላምፓርድ ለክለቡ ባለፉት ሰባት አመታት ውስጥ የቀጠረው ሰባተኛው አሰልጣኝ ሆኗል።

አዲሱ ስራውም ቀላል እንደማይሆን ነገርገረን ለሱ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ተናግሯል።


ኤቨርተን ማርኮ ሲልቫን በአሰልጣኝነት ቀጠረ

ዴቪድ ሞይስ ከለቀቁ በኋላ አሰልጣኞችን እየቀያየረ የሚገኘው ኤቨርተን ፖርቹጋላዊውን ማርኮ ሲልቫን ቀጥሯል።

ክለቡ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ሮናልድ ኩማንን ካሰናበተ በኋላ ሳም አላርዳይስን በጊዚያዊነት ከቀጠረ ከስድስት ወራት በኋላ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ማሰናበቱ ይታወሳል።

በምትካቸውም ማርኮ ሲልቫን የሶስት አመታት ኮንትራት በመስጠት አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ አድርጓል።

አሰልጣኙም ከሀል ሲቲ እና ከዋትፎርድ በመቀጠል ሶስተኛ የእንግሊዝ ክለባቸውን ለማሰልጠን ተረክበዋል።

“አዲሱ የኤቨርተን አሰልጣኝ በመሆኔ በጣም ኩራት ይሰማኛል።ይህንን ትልቅ ሀላፊነት በመረከቤ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል

“ለክለቡ ባለቤት ፋርሀድ ሞሺር፣የክለቡ ሊቀመንበር እና ቦርድ ላመሰግን እፈልጋለው።የክለቡ ትልቅ ታሪክን እንዲሁም ደጋፊው የሚፈልገውን አውቃለው።” ሲሉ ማርኮ ሲልቫ ተናግረዋል።


ሰንደርላንድ አዲስ አሰልጣኝ ቀጠረ

ከክሪስ ኮልማን ጋር የተለያየው እና ወደ ሊግ አንድ የወረደው ሰንደርላንድ የስኮትላንዱን ሴንት ሚረን አሰልጣኝ የነበሩት ጃክ ሮስን ቀጥሯል።

ሰንደርላንድ በሁለት አመታት ውስጥ ከፕሪምየርሊጉ ተንሸራቶ ወደ እንግሊዝ ሶስተኛ ሊግ[ሊግ አንድ] ወርዷል።

አሰልጣኙ ከባርንስሌ እና ኤፕስዊች ጋር ግኑኝነት ፈጥረው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ምርጫቸው ስታድየም ኦፍ ላይት አድርገዋል።

“የዚህን ክለብ ታሪክ፣አደረጃጀት፣የደጋፊ መሰረት ስትመለከቱ ይህ ክለብ ምን ማለት እንደሆነ ትረዳላችሁ።የዚህ ክለብ አባል ስለሆንኩ እና የክለቡ አቅም ሳገናዝብ በደስታ እሞላለው።” ሲሉ አዲሱ አሰልጣኝ ተናግረዋል።